መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 4
4
1እርሱም አለኝ፥ “መጀመሪያ በሰው ልጅ ነው፤ በኋላ ግን እኔ ራሴ ነኝ፤ ሰማይና ምድር፥ ሀገሮችም ሳይፈጠሩ፥ የዓለም መንገድም ሳይጸና፥ ነፋሳትም ሳይነፍሱ፤ 2የነጐድጓድ ድምፅም ሳይሰማ፥ የመብረቅ ብልጭታም ሳይበራ፥ የገነት ምድር ሳይፈጠር፥ 3የአበቦችም ውበት ሳይታይ፥ የመሬት መነዋወጥ ኀይልም ሳይጸና፥ የመላእክትም ሠራዊት ሳይቈጠሩ። 4የሰማይም ምጥቀቱ ሳይታይ፥ የሰማያትም መስፈርት ሳይሰፈር፥#አንዳንድ ዘርዕ “የጽዮን ተራራ የእግሬ መረገጫ ሁና ከመመረጥዋ በፊት” የሚል ይጨምራል። 5የሚመጣው ዓለም ፍለጋ ሳይታወቅ፥ የኃጥኣን ጥላ ሳይወገድ፦ የጌታ ማኅተም ሕግን በሚጠብቁና ሃይማኖትን በሚያምኑ ላይ ሳይታተም፥ 6ያንጊዜ እኔ ራሴ ይህን ዓለም እጐበኝ ዘንድ አሰብሁ፤ ሌላም አይደለም።”
7መልሼም እንዲህ አልሁት፥ “የመጀመሪያው ዓለም ምልክቱ፥ ጊዜውስ ምንድን ነው? ፍጻሜውስ መቼ ነው? የሁለተኛውስ ዓለም መጀመሪያው መቼ ነው?” 8እንዲህም አለኝ፥ “ከአብርሃም እስከ ይስሐቅ ነው፤ ያዕቆብና ዔሳው ከእርሱ ተወልደዋል፥ በተወለዱም ጊዜ ያዕቆብ የኤሳውን ተረከዝ ይዞ ተወለደ። 9ኤሳው የዚህ ዘመን ፍጻሜ ምሳሌ ነው፤ ያዕቆብም የአዲሱ ዘመን መጀመሪያ ነው። 10የሰው መጨረሻ አካሉ ተረከዙ ነውና፤ የሰውም መጀመሪያ አካሉ እጁ ነው። ነገር ግን ዕዝራ አትመራመር።”
11እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ በዐይኖችህ ፊት ባለሟልነትንስ ካገኘሁ፥ 12ባለፈው ሌሊት አስቀድሞ በከፊል የነገርኸኝን የዚህን ምልክት መጨረሻ ለባሪያህ ንገረው።” 13እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ ጩኸት የተመላበትንም ቃል እነግርሃለሁ። 14አንተ በውስጡ የቆምህበት ቦታ ቢነዋወጥ በነገርሁህ ጊዜ አትደንግጥ፤ ስለ ነገር መጨረሻ ነውና። 15ያንጊዜ የምድር መሠረቶች ነገርን ያስረዳሉ። 16ነገሩ ስለ እነርሱ ነውና፥ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይነዋወጣሉም፤ በመጨረሻቸው ያልፉ ዘንድ አላቸውና፥”
17ከዚህም በኋላ ይህን በሰማሁ ጊዜ ተነሥቼ በእግሮች ቆምሁ፤ እነሆ፥ የሚናገረውንም ቃል ሰማሁ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ ነበር። 18በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ይጐበኛቸው ዘንድ ልዑል በደረሰ ጊዜ እነሆ፥ ዘመን ይመጣል ይል ነበር። 19ጽዮን በታነጸች ጊዜ ያመፁብኝን ዐመፃቸውን ያንጊዜ እመራመራቸው ዘንድ አለኝ። 20ይመጣ ዘንድ ያለው ዓለም በታተመ ጊዜ የማደርገው ምልክት ይህ ነው፤ በሰማይ መጻሕፍት ይገለጣሉ፤ ሁሉም ያየኛል። 21ዓመት የሆናቸው ሕፃናት ፈጽመው ይናገራሉ፤ የፀነሱ ሴቶችም የሦስት ወርና የአራት ወር ሕፃናትን ይወልዳሉ፤ ሕያዋንም ሆነው ይነሣሉ። 22የማትታይ ምድርም ዘርዕ ተዘርቶባት ትታያለች፥#“ዘር ተዘርቶባት የነበረች ምድር እንደ አልተዘራባት ትሆናለች” የሚል ዘርዕ ይገኛል። ውስጣቸው ሙሉ የነበሩ ቤቶችም ባዷቸውን ይገኛሉ። 23ነጋሪት ይሰማል፤ የሰማውም ሁሉ ይደነግጣል። 24በእነዚያም ወራት ወዳጆች ከወዳጆቻቸው ጋር እርስ በርሳቸው እንደ ጠላት ይዋጋሉ። ምድርም በውስጧ የሚኖሩባትን ታስደነግጣቸዋለች፤ የውኃው ምንጮችም ይገታሉ፤ እስከ ሦስት ሰዓትም ድረስ አይፈስሱም።
25“ከዚህ ከነገርሁህ ሁሉ የቀረ ሰው ሁሉ የሚድን እርሱ ነው፤ ትድግናዬን የዘመኔንም ፍጻሜ የሚያይ እርሱ ነው። 26ያንጊዜም ያረጉና ከተወለዱ ጅምሮ ሞትን ያልቀመሱ እነዚያን ሰዎች ያዩአቸዋል፤ በዓለም የሚኖሩ ሰዎችም ልቡና ይለወጣል፤ ሌላ ልቡናም ይሰጣቸዋል። 27ክፋት ትደመሰሳለችና፥ ተንኰልም ትጠፋለችና። 28ሃይማኖት ትለመልማለች፤ ሞት ድል ይነሣል፤ ያለ ፍሬ ለብዙ ዘመን የነበረች ጽድቅ ትገለጣለች።”
29በተናገረኝም ጊዜ እኔ የቆምሁበት ስፍራ ጥቂት ጥቂት እያለ ይነዋወጥ ነበር። 30እርሱም አለኝ፥ “ባለፈችው ሌሊት እንደ ነገርሁህ ይህን ምልክት እነግርህ ዘንድ መጣሁ። 31ዳግመኛ ሰባት ቀን ብትጾምና ብትጸልይ ከዚህ የሚበልጥ ዳግመኛ እነግርሃለሁ። 32ቃልህ በልዑል ዘንድ መሰማትን ተሰምትዋልና። ከሕፃንነትህም ጀምሮ ያለው የጽድቅህ ኀይል ተገልጧልና። 33ስለዚህም ይህን ነገር እነግርህ ዘንድ ልዑል ላከኝ። 34እንዲህም አለኝ፦ እመን፤ አትፍራ፤ በኋላ ዘመን እንዳትጠራጠር ስለ ቀደመውም ክፉ አሳብህ አትቸኩል።”
ሦስተኛው ራእይ
35ከዚህም በኋላ የነገረኝን ሦስቱን ሱባዔያት እጨርስ ዘንድ ዳግመኛ ሰባት ቀን እያለቀስሁ ጾምሁ። 36በዚያች#አንዳንድ ዘርዕ “በስምንተኛይቱ” ይላል። ሌሊት ልቤ ታወከችብኝ፤ በልዑልም ፊት እናገር ጀመርሁ። 37ሰውነቴ ፈጽማ ትናደዳለችና፥ ልቡናዬም ትናወጣለችና።
38እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ በመጀመሪያው መፍጠርህ በመጀመሪያዪቱ ቀን ሰማይና ምድር ይፈጠር አልህ፤ እንዲሁም ተፈጠረ፤ ቃልህም ፍጥረትን ይፈጥር ነበር። 39መንፈስም ይሰፍፍ ነበር። ጨለማም ሞልቶ ነበር፥ ፀጥ ብሎም ነበር። ድምፅም አልነበረም፤ የሰው ልጅ ድምፅ ገና አልነበረምና። 40ያንጊዜም ብርሃን ከአዳራሽህ እንዲገኝ ፍጥረትህም እንዲገለጥ አዘዝህ።
41“ዳግመኛም በሁለተኛው ቀን በሰማያት ያለ ነፋስን ፈጠርህ፤ እኩሌታውም ወደ ላይ ይወጣ ዘንድ፥ እኩሌታውም በታች ይኖር ዘንድ በውኃው መካከል እንዲለይ አዘዝኸው። 42ዳግመኛም በሦስተኛው ቀን ውኃውን ከምድር በሰባተኛው እጅ ላይ እንዲሰበሰብ አዘዝኸው። የምድር ስድስቱ እጅም በውስጣቸው ያርሱ ዘንድ፥ ዘርም ይዘሩ ዘንድ፥ በፊትህም ይኖሩ ዘንድ ደረቅ ሆኖ ይቅር አልህ። 43ቃልህም በወጣ ጊዜ ፍጥረት ይፈጠር ነበር። 44ያንጊዜም ቍጥር የሌለው ብዙ ፍሬ በቀለ፤ የሁሉም ጣዕሙ፥ ያበባውም መልክ ልዩ ልዩ ነበር፤ የእንጨቱም ዓይነት ልዩ ልዩ ነበር፤ መዓዛውም ልዩ ልዩ ነበር።
45“ባራተኛይቱም ቀን ያበሩ ዘንድ የጨረቃና የፀሐይ ብርሃን፥ የከዋክብትም ሥርዐት ይፈጠር ዘንድ አዘዝህ። 46ይፈጠር ዘንድ ላለው ሰውም ያገለግሉ ዘንድ አዘዝሃቸው።
47“ባምስተኛውም ቀን የናጌብ ውኃ ያለበትን ያን ሰባተኛውን እጅ ሕይወት ያላቸውን ወፎችንና ዓሣዎችን ያስገኝ ዘንድ አዘዝኸው። 48ስለዚህ ትውልድ ሁሉ ጌትነትህን ይናገሩ ዘንድ የማይናገርና ደመ ነፍስ የሌለው ያ ውኃ ሕይወት ያለውን አስገኘ። 49ያንጊዜም የፈጠርሃቸውን ሁለቱን እንስሳት ጠበቅህ፤ ያንዱን ስሙን ብሔሞት አልኸው፤ የሁለተኛውንም ስሙን ሌዋታን አልኸው። 50በየራሳቸውም ለየሃቸው፤ የናጌብ#“ናጌብ” በሌሎች ዘሮች አይገኝም። ውኃ ያለበት ያ ሰባተኛው እጅ ሊወስናቸው አይችልምና፥ 51አራቱ#“አንድ ሽህ” የሚልም ይገኛል። ተራሮች ባሉበት በዚያ እርሱ በውስጡ ይኖር ዘንድ ለብሔሞት ከስድስቱ እጅ አንዱን እጅ የብስን ሰጠኸው።
52“ለሌዋታንም የባሕሩን ሰባተኛ እጅ ሰጠኸው፤ ለምትወዳቸው ምግብ ይሆኑ ዘንድም ጠበቅሃቸው። 53በስድስተኛዪቱም ቀን በፊትህ እንስሳን፥ የሰማይ ወፎችንና የዱር አውሬዎችን ታስገኝ ዘንድ ምድርን አዘዝሃት። 54በዚህም ሁሉ ላይ አዳምን ገዥ አድርገህ ሾምኸው፤ አስቀድመህ በፈጠርኸው ፍጥረት ላይም ገዥ ሆነ። በእርሱም ምክንያት የመረጥኸን እኛ ወገኖችህ ከእርሱ ተገኘን።
55“አቤቱ፥ ይህን ሁሉ በፊትህ ተናገርሁ፤ ይህን ዓለም ሰለ እናንተ ፈጠርሁት ብለሃልና። 56ከአዳም የተወለዱ ሌሎች አሕዛብ ግን እንደ ኢምንት ናቸው፤ እንደ ምራቅም ይመስላሉ፤ እንደ አፍሻት ጠብታም ናቸው፤ ደስታቸውም እንደ ኢምንት ነው። 57አሁንም እነሆ እንደ ኢምንት ናቸው ያልሃቸው እነዚያ አሕዛብ እነሆ በእኛ ላይ ሠለጠኑ፤ ረገጡንም። 58የምወደው የበኸር አንድያ ልጄ ያልኸን እኛ ወገኖችህ ግን በአሕዛብ እጅ ገባን። 59ነገር ግን ዓለምን ስለ እኛ ከፈጠርኸው ዓለማችንን ለምን አንወርስም? ይህስ እስከ መቼ ድረስ ነው?”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ