ትንቢተ ሶፎንያስ 1
1
1 #
2ነገ. 22፥1—23፥30፤ 2ዜ.መ. 34፥1—35፥27። በይሁዳ ንጉሥ በአሞን ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ፥ ወደ አማርያ ልጅ፥ ወደ ገዳልያ ልጅ፥ ወደ ኩሺ ልጅ፥ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የጌታ ቃል ይህ ነው።
በይሁዳ ላይ የሚመጣው ፍርድ
2“ሁሉን ነገር ከምድረ ገጽ ፈጽሜ አጠፋለሁ” ይላል ጌታ። 3ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሦች አጠፋለሁ፥ ክፉዎች እንዲደናቀፉ አደርጋለሁ፥ ሰውንም ከምድር ገጽ እቆርጣለሁ ይላል ጌታ። 4እጄንም በይሁዳ ላይና በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፥ ከዚህም ስፍራ የበዓልን ትሩፍና የጣዖታቱን ካህናት ስም ከካህናቱ ጋር እቆርጣለሁ፤ 5በሰገነትም ላይ ለሰማያት ሠራዊት የሚሰግዱትን፥ ለጌታ የሚሰግዱትንና በእርሱም የሚምሉትን፥ በንጉሣቸውም ደግሞ የሚምሉትን፥ 6ጌታን ከመከተል የተመለሱትን፥ ጌታን ያልፈለጉትንና ያልጠየቁትን አጠፋለሁ።
7በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ! የጌታ ቀን ቀርቧልና፤ ጌታ መሥዋዕትን አዘጋጅቷል የጠራቸውንም ቀድሶአል። 8በጌታ የመሥዋዕት ቀን ባለ ሥልጣኖችንና የንጉሡን ልጆች፥ እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እበቀላለሁ። 9በዚያን ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፥ የጌታቸውን ቤት በዓመፅና በማታለል የሚሞሉትን እቀጣለሁ።
10በዚያ ቀን ይላል ጌታ፥ “የዓሣ በር” የጩኸት ድምፅ፥ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ዋይታ፥ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል። 11እናንተ በመክቴሽ የምትኖሩ ሆይ አልቅሱ፥ የከነዓን ሕዝብ ሁሉ ይጠፋሉና፥ ብርም የሚመዝኑ ሁሉ ይቆረጣሉና። 12በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እፈትሻለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚረጉትን፥ በልባቸውም፦ “ጌታ መልካምም ክፉም አያደርግም” የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ። 13ሀብታቸው ይዘረፋል፥ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፥ ነገር ግን አይኖሩባቸውም፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም።
ታላቁ የጌታ ቀን
14ታላቁ የጌታ ቀን ቀርቧል፤ የጌታ ቀን ድምፅ ቀርቧል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ ምርር ብሎ ይጮኻል። 15ያ ቀን የመዓት ቀን የጭንቀትና የሥቃይ ቀን፥ የጥፋትና የመፍረስ ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥ 16በተመሸጉ ከተሞችና በረጃጅም ግንቦች ላይ መለከትና ቀረርቶ የሚሰማበት ቀን ነው። 17በሰዎች ላይ ጭንቀትን አመጣለሁ፤ እንደ ዕውርም ይሄዳሉ፥ በጌታ ላይ ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ ደማቸው እንደ ትቢያ ይፈስሳል፥ ሥጋቸውም እንደ ጉድፍ ይጣላል። 18በጌታ የመዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች፥ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ አስፈሪ ፍፃሜ ያመጣባቸዋልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ሶፎንያስ 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ