ትንቢተ ዘካርያስ 14

14
የኢየሩሳሌም ውድቀት እና ትድግና
1እነሆ፥ ከእናንት የተወሰድ ምርኮ በመካከላችሁ ለክፍፍል የሚበቃበት የጌታ ቀን ይመጣል። 2አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ እንዲነሱ እሰበስባቸዋለሁ፤ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማይቱም እኩሌታ ለምርኮ ይጋዛል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዋ አይፈናቃልም። 3#ኢሳ. 31፥4።ጌታም ይወጣል፥ በጦርነትም ቀን እንደሚዋጋ ከእነዚያ አሕዛቦች ጋር ይዋጋል። 4#ሚክ. 1፥4።በዚያም ቀን የእግዚአብሔር እግሮች በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም በመካከሉ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ጥልቅ ሸለቆ ይሆናል፤ የተራራውም እኩሌታ ወደ ሰሜን፥ እኩሌታውም ወደ ደቡብ ይሸሻል። 5#አሞጽ 1፥1፤ ዘዳ. 33፥2-3፤ ማቴ. 16፥27፤ 1ተሰ. 3፥13።የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ስለሚደርስ፥ በተራሮች መካከል ባለው ሸለቆ ትሸሻላችሁ። በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት ከሆነው ሽሽት በበለጠ ትሸሻላችሁ። ከዚያም አምላኬ ጌታ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል።
የኢየሩሳሌም መታደስ
6በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ አይኖርም። 7የማያቋርጥ አንድ የብርሃን ቀን ይሆናል፥ እርሱም በጌታ ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። 8#ዘካ. 13፥1፤ ሕዝ. 47፥1-8።በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፥ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይወርዳል፤ ይህ በበጋና በክረምት የማያቋርጥ ይሆናል። 9#መዝ. 96፥7-10፤ 97፥1፤ 98፥4-6፤ ራእ. 11፥15።ጌታም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን ጌታ አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል። 10ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ፥ እንደ ዓረባ ትሆናለች፤ እርሷም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው የበሯ ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች። 11#ዘዳ. 33፥28፤ ኤር. 31፥40፤ ራእ. 22፥3።ከተማዋም ሰዎች ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይኖርም። ኢየሩሳሌምም በሰላም ትኖራለች።
የኢየሩሳሌም ጠላቶች ዕጣ
12 # ኢሳ. 66፥24። ጌታም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፤ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዐይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። 13#1ሳሙ. 5፥9፤ 11፤ 14፥18-20፤ ኢሳ. 22፥5።በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር የመጣ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ያድራል፤ እርስ በእርሳቸውም ይያያዛሉ፥ አንዱም በሌላው ላይ ይነሣል። 14ይሁዳም እንኳን ኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ለውጊያ ይነሣባታል። በዙሪያም ያሉትን የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፥ እጅግ ብዙ ወርቅና ብር፥ ልብስም ይሰበሰባል። 15በፈረሶች፥ በበቅሎዎች፥ በግመሎች፥ በአህዮች፥ እንዲሁም በዚያም ሰፈር ባሉ እንስሶች ሁሉ ላይ በሰዎች ላይ እንደ ሆነው ዓይነት ቸነፈር በእነርሱም ላይ ይሆናል።
የኢየሩሳሌም፥ አይሁድና አሕዛብ መጪው ጊዜ
16 # ዘሌ. 23፥33-36፤ ዘዳ. 16፥13-15። በኢየሩሳሌም ላይ ከመጡት ከአሕዛብ ሁሉ የቀሩት ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለመስገድ፥ የዳስ በዓልንም ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ። 17#ዘካ. 8፥20-23፤ ኢሳ. 2፥1-4፤ ሚክ. 4፥1-3።ከምድርም ወገኖች ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ለማይወጡ ለእነርሱ ዝናብ አይዘንብላቸውም። 18#ዘፀ. 5፥3፤ 9፥15።የግብጽም ወገን ባይወጣ ወደዚያም ባይሄድ፥ ጌታ የዳስ በዓልን ለማክበር የማይወጡትን አሕዛብ የሚቀሥፍበት ቸነፈር በእርሱ ላይ ይመጣል። 19ይህ የግብጽ ቅጣት ይሆናል፥ የዳስ በዓልንም ለማክበር የማይወጡት አሕዛብ ሁሉ ቅጣት እንደዚህ ይሆናል። 20#ዘሌ. 23፥20፤ 27፥30፤32።በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኩራ ላይ፦ “ለጌታ የተቀደሰ” ተብሎ ይጻፋል። በጌታም ቤት ያሉ ምንቸቶች በመሠዊያው ፊት እንዳሉ ዳካዎች ይሆናሉ። 21በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶችም ሁሉ ለሠራዊት ጌታ የተቀደሱ ይሆናሉ። የሚሠውትም ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ፥ በእነርሱም ውስጥ ይቀቅሉባቸዋል። በዚያም ቀን በሠራዊት ጌታ ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ነጋዴ አይገኝም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ