መጽሐፈ ጦቢት 7
7
1ወደ ኤቅባጥና ከተማ በገቡ ጊዜ ጦብያ “ወንድሜ አዛርያ በቀጥታ ወደ ወንድማችን ወደ ራጉኤል ቤት ውሰደኝ” አለው። እሱም ወደ ራጉኤል ቤት ወስደው፤ ራጉኤልም በግቢው አጥር በር አጠገብ ተቀምጦ አገኙት፤ እነርሱ አስቀድመው ሰላምታ አቀረቡለት። እርሱም “እንደምናችሁ ወንድሞቼ፥ እንኳን ደኀና መጣችሁ” አለና ወደ ቤቱ አስገባቸው። 2ሚስቱ ኤድናን “ይህ ወጣት ወንድሜ ጦቢትን እንዴት ይመስላል!” አላት። 3ኤድናም “ወንድሞቼ ከየት ነው የመጣችሁት?” አለቻቸው። እነርሱም “ወደ ነነዌ ከተሰደዱት ከኒፍታሊ ልጆች መካከል ነን” አሏት። 4እርሷም “ወንድማችን ጦቢትን ታውቁታላችሁን?” አለቻቸው። እነርሱም “አዎን እናውቀዋለን” አሏት። እርሷም “እንዴት ነው?” አለቻቸው። 5እነርሱም “በሕይወት አለ፤ ደኀና ነው” አሏት። ጦብያም ቀጠል አድርጎ “አባቴ ነው” አለ። 6#ዘፍ. 33፥4፤ 45፥14፤ ሉቃ. 15፥20።በዚያን ጊዜ ራጉኤል ብድግ አለና ሳመው፥ አለቀስም። 7ቀጥሎም “ተባረክ ልጄ! የደግ አባት ልጅ ነህ። እንዲህ ያለ ብሩህና መልካም የሚሠራ ሰው ዐይኖቹን ማጣቱ እንዴት ያሳዝናል” አለ። በዘመዱ ጦቢያ አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ። 8ሚስቱ ኤድናም ስለ እርሱ አለቀሰች፥ ልጃቸው ሣራም አለቀሰች። 9ከዚህ በኋላ ራጉኤል አንድ የበግ ሙክት አርዶ መልካም መስተንግዶ አደረገላቸው። ታጠቡና ለመብላት በማዕድ ተቀመጡ፥ ጦብያ ሩፋኤልን “ወንድሜ አዛርያ ዘመዴ የሆነችውን ሣራን እንዳገባ ራጉኤልን ጠይቀው” አለው። 10ራጉኤል ንግግሩን ሰምቶ ወጣቱን እንዲህ አለው፦ “ብላ፥ ጠጣ ዛሬ ማታ ተደሰት፤ ወንድሜ ሆይ ልጄ ሣራን ካንተ በቀር ሌላ ሊያገበት መብት የለውም፤ እኔ እንኳን ልሰጣተ ብፈልግ አንተ የቅርብ ዘመዷ ስልሆንህ ላንተ እንጂ ለሌላ ልሰጣት አልችልም። ነገር ግን ልጄ ሆይ እውነቱን ልንገርህ፥ 11ከዚህ ቀደም ከወገኖቻችን መካከል ከሰባት ሰዎች ጋር አጋብቻት ነበር፤ ሁሉም በመጀመሪያው ቀን ማታ ወደ ክፍሏ ሲገቡ ሞቱ። ለአሁን ግን ልጄ ብላ፥ ጠጣ፥ ጌታ ጸጋውንና ሰላሙን ይሰጥሃል።” ጦብያም “የእኔን ነገር እስክትወስንልኝ ምንም አልበላም፥ አልጠጣም” አለ። ራጉኤልም እንዲህ አለው “መልካም፤ በሙሴ መጽሐፍ መሠረት ለአንተ ተሰጥታለች፥ ለአንተ እንድትሰጥ ሰማይ እራሱ ደንግጓል፥ ስለዚህ እኀትህን ለአንተ ሰጥቻታለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ ወንድሟ ነህ፥ እርሷም እኀትህ ናት። ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም ለአንተ ተሰጥለች። ልጄ የሰማዩ ጌታ በዚህች ሌሊት ሞገስ ይሁናችሁ፤ ጸጋውንና ሰላሙን ይስጣችሁ።” 12ከዚህ በኋላ ራጉኤል ልጁን ሣራን ጠራትና መጣች፤ በእጇም ያዛትና ለጦብያ እንዲህ በማለት ሰጠው “ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ሕጉና በሙሴ መጽሐፍ የተጻፈው ውሳኔ ሚስት አድርጎ ሰጥቶሃል፤ ውሰዳት፥ ወደ አባትህም ቤት በደኅና አድርሳት፤ የሰማይ አምላክ በሰላም ያድርሳችሁ።” 13ቀጥሎም እናቷን ጠራና የሚጽፍበትን ወረቀት እንድትሰጠው ጠየቃት። የሙሴ መጽሐፍ በደነገገው መሠረት ሚስቱ እንድትሆን የጋብቻውን ውል ጽፎ ሰጠው። 14ከዚህ በኋላ መብላትና መጠጣት ጀመሩ። 15ራጉኤል ሚስቱን ኤድናን ጠራና “እኀቴ ሁለተኛውን ክፍል አዘጋጂና እርሷን ወደዚያ ውሰጀት” አላት። 16እርሷም እንዳላት ሄዳ በዚሁ ክፍል አልጋውን አዘጋጀች። ልጅቷንም ወደዛ ወሰደቻት፤ ማልቀስም ጀመረች፥ ዕንባዋንም ጠረገችና፦ 17“በርቺ ልጄ፥ የሰማዩ ጌታ ኀዘንሽን ወደ ደስታ ይለውጠው፥ አይዞሽ ልጄ” ብላት ወጣች።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጦቢት 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ