መጽ​ሐፈ ጦቢት 6

6
የጦቢት ልጅ ጉዞ
ዓሣው
1እርሷም ማልቀስዋን ተወች። 2ልጁም ከመልአኩ ጋር ሄደ፥ ውሻውም ከኋላ ተከትሎአቸው ሄደ፥ ሲሄዱ ዋሉና ሲመሽ በጢግሮስ ወንዝ አጠገብ አረፉ። 3ልጁ እግሩን ሊታጠብ ወደ ወንዝ ወረደ፥ አንድ ትልቅ ዓሣም ከውሃው ውስጥ ዘሎ በመውጣት እግሩን ሊውጠው ተወረወረ፤ ልጁም ጮኸ። 4መልአኩም “ዓሣውን ያዘው አትልቀቀው” አለው። ልጁም ዓሣውን ይዞ እየጐተተ ወደ ባህሩ ዳር አወጣው። 5መልአኩም “ዓሣውን እረደውና ሐሞቱን፥ ልቡንና ጉበቱን አውጣው፤ እነዚህን ያዝና የሆድ እቃውን ወዲያ ጣለው፤ ሐሞቱ፥ ልቡና ጉበቱ ለመድኃኒትነት ይጠቅማልና” አለው። 6ልጁ ዓሣውን ቀዶ ከፈተውና ሐሞቱን፥ ልቡንና ጉበቱን ወሰደ፥ ከዚህ በኋላ ዓሣውን ጠበሰና በሉት፤ የቀረውን ለጉዞ በጨው ቀመመው፤ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ወደ ሜዶንም ተቃረቡ። 7ከዚህ በኋላ ልጁ መልአኩን እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ወንድሜ አዛርያ የዓሣው ልብ ጉበትና ሐሞት ምን ለመፈወስ ይጠቅማል?” 8እሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የዓሣውን ልብና ጉበት ጋኔን ወይም ክፉ መንፈሰ በያዘው ወንድ ወይም ሴት ፊት ካጨስከው በሽታው ይለቃቸዋል፥ አይመለስባቸውምም። 9ሐሞቱ ግን ዐይኖቹ ላይ ብልዝ ለጣለበት ሰው በቅባትነት ያገለግላል፥ ከተጠቀምክ በኋላ እፍ ብትለው ብልዞቹ ይጠፋሉ።” 10ወደ ሜዶን ደረሱ፥ ወደ አቅባጥናም ተቃረቡ። 11ሩፋኤል ልጁን “ወንድሜ ጦብያ” አለው። እርሱም “አቤት” አለው። መልአኩም ቀጠለና “ዛሬ ሌሊት ማደር የሚገባን በዘመድህ በራጉኤል ቤት ነው፥ ሣራ የምትባል ልጅ አለችው፤ 12ከሣራ በቀር ሌላ ልጅ የለውም፥ የእርሷ የቅርብ ዘመድዋ አንተ ነህ፥ እርሷን ለማግባትና የአባትዋን ሀብት ለመውረስ ከማንም በላይ መብት ያለህ አንተ ነህ፤ እርሷም አዋቂ፥ ብርቱና መልከ መልካም ናት፥ አባትዋም በጣም ይወዳታል 13አንተ እርሷን ለማግባት መብት አለህ፥ ስማኝ ወንድሜ፥ ይህች ልጃገረድ ያንተ እጮኛ እንድትሆን ዛሬውኑ ለአባትዋ እኔ እናገራለሁ፥ ከራጌስ ስንመለስ ሰርጉን እንደግሳለን፥ ራጉኤል አንተን ከልክሎ ለሌላ ሊድራት እንደማይችል አረጋግጥልሃልሁ፥ ምክንያቱም ልጅቷን ላንተ መዳር እንደሚገባው እያወቀ ለሌላ ሰው ቢድራት በሙሴ መጽሐፍ መሠረት በሞት ይቀጣል። ስለዚህ ወንድሜ ምክሬን ስማ፥ ዛሬ ማታ ስለ ልጅቷ ተነጋግረን ለጋብቻ እንጠይቃታለን፥ ከራጌስ ስንመለስ ከእኛ ጋር ወደ ቤት ይዘናት እንሄዳለን።” 14ጦብያ ለሩፋኤል እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ወንድሜ አዛርያ እስዋ ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ባል እንዳገባችና ሰባቱም ባሎችዋ በሰርጉ ቀን ወዳለችበት ጫጉላ ሲገቡ እንደሞቱ ሰምቻለሁ። ወደ እርሷ በገቡበት በዚያች ሌሊት ይሞታሉ። የገደላቸውም አንድ ጋኔን መሆኑን ሰምቻለሁ። 15እኔም ፈርቻለሁ፤ ጋኔኑ ስለሚወዳት እርሷን አይጐዳትም፥ ወደ እርሷ መቅረብ የሚፈልገውን ሰው ግን ወዲያውኑ ይገድለዋል። እኔም ለአባቴ አንድ ልጅ ነኝ መሞትም አልፈልግም፥ አባትና እናቴ በቀሪው ዘመናቸው ሁሉ በእኔ እያዘኑ እንዲኖሩ አልፈልግም። የሚቀብራቸውም ሌላ ልጅ የላቸውም።” 16መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ከአባትህ ወገን የሆነች ሴት እንድታገባ ብሎ አባትህ የመከረህን ረሳኸው? ስማኝ ወንድሜ! ስለ ጋኔኑ እንደሆነ አትጨነቅ፥ አግባት፤ ዛሬ ማታ ሚስት እንድትሆንህ እንደሚሰጡህ አውቃለሁ። 17ስለዚህ ወደ ጫጉላው ቤት ከገባህ በኋላ፥ ከዓሣው ጉበትና ልብ ጥቂት ወስደህ በዕጣን ማጨሻ ላይ አድርገው፤ 18ጋኔኑ ጭሱ ሲሸተው ሽሽቶ ይሄዳል ወደ እርሷም ከቶ ተመልሶ አይመጣም። አብራችሁ ከመተኛታችሁ በፊት ሁለታችሁም ለመጸለይ ተነሱ፥ የሰማዩ ጌታ ጸጋውንና ከለላውን እንዲሰጣችሁ ለምኑት። አትፍራ! ከጥንት ጀምሮ እርሷ የተወሰነችው ለአንተ ነው፥ የምታድናትም አንተ ነህ። ቃሌን እሰጥሃለሁ እርሷ አንተን ትከተላለች፥ እንደ ወንድሞች የሚሆኑልህ ልጆችንም ትወልድልሃለች፥ አትጨነቅ።” ጦቢያ የሩፋኤልን ንግግር ባደመጠ ጊዜና እርሷ ከዘሩና ከአባቱ ወገን የሆነች እኀቱ መሆንዋን ባወቀ ጊዜ በጣም ወደዳት፥ ልቡም ከእርሷ ጋር ሆነ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ