መጽሐፈ ጦቢት 5
5
ሩፋኤል
1ከዚህ በኋላ ጦብያ ለአባቱ ለጦቢት እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አባቴ ያዘዝኸኝን ሁሉ እፈጽማለሁ። 2ግን ሰውዬው አያውቀኝም እኔም አላውቀውም ይህን ገንዘብ ከእሱ እንዴት ማግኘት እችላለሁ? እንዲያውቀኝና እንዲያምነኝ ገንዘቡንም እንዲሰጠኝ ምን ምልክት እሰጠዋለሁ? ወደ ሜዶን የሚወስደውንም መንገድ አላውቀውም።” 3ጦቢት ለልጁ ለጦብያ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንድ ወረቀት ፈርመልኝ፤ እኔም እዚያው ላይ ፈርሜአለሁ የተፈረመውን ወረቀት በሁለት ገምሼ ከገንዘቡ ጋር አድርጌዋለሁ። ይህን ገንዘብ ከሰውዬው ዘንድ ካስቀመጥሁ አሁን ሃያ ዓመት ሆኖአል። እንግዲህ ልጄ ሆይ የሚከተልህ አንድ የታመነ የመንገድ ጓደኛ ፈልግ፤ ወስዶ ሲመልስህ ደሞዙን እንከፍለዋለን፤ ሂድና ገንዘብ ከገባኤል ተቀበል።”
ጦቢት
4 #
ዕብ. 13፥2። ጦቢያ ወደ ሜዶን መንገዱን የሚያውቅና ከእርሱም ጋር የሚሄድ ሰው ለመፈለግ ወጣ። ጦብያ ሲወጣ ከፊት ለፊቱ መልአኩ ሩፋኤል ቆሞ አገኘው፤ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ግን አላወቀም። 5“ከወዴት ነህ ወንድሜ?” አለው። እርሱም “እኔ ከወገኖችህ የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ፤ እዚህ የመጣሁት ለመሥራት ነው” አለው። ጦብያም “ወደ ሜዶን የሚወስደውን መንገድ ታውቀዋለህን?” አለው። 6ሌላኛውም “አዎን አውቀዋለሁ፥ ብዙ ጊዜ ወደዚያ ተመላልሻለሁ፤ መንገዶቹን ሁሉ ደኀና አድርጌ አውቃቸዋለሁ፥ ብዙ ጊዜ ወደ ሜዶን ሄጃለሁ፥ የማርፈውም በሜዶን አገር በራጌስ በሚኖረው ወንድማችን በሆነው በገባኤል ቤት ነው፤ ከኤቅባጥና ወደ ራጌስ ሁለት ቀን ያስኬዳል፥ ምክንያቱም ራጌስ የምትገኘው በተራራው ላይ ሲሆን ኤቅባጥና ደግሞ በሜዳው መሃል ነው።” 7ጦብያ “አባቴን ነግሬው እስክመጣ ቆየኝ ወንድሜ፤ አንተ ከእኔ ጋር እንድትመጣ እፈልጋለሁ፥ ደሞዝህንም እከፍልሃለሁ” አለው። 8እርሱም “መልካም፥ እጠብቅሃለሁ፤ ግን እንዳትቆይ” አለው። 9ጦብያም ለአባቱ ለመንገር ወደ ቤት ገባና “እነሆ ከወንደሞቻችን ከእስራኤላውያን አንድ ሰው አግኝቻለሁ” አለው። ጦቢትም “ከየትኛው ቤተሰብና ነገድ መሆኑን ለማወቅና የመንገድ ጓደኛህ ለመሆን እምነት የሚጣልበት መሆኑን ለመገንዘብ እስቲ ሰውዬውን ጥራልኝ ልጄ ሆይ” አለው። ጦብያም ሊጠራው ወጣና “ወንድሜ አባቴ ሊያይህ ይፈልጋል” አለው። 10መልአኩ ወደ ቤት ገባ፤ ጦቢትም አስቀድሞ ሰላምታ ሰጠው፤ እርሱም “መልካም ነገር እመኝልሃለሁ” ሲል መለሰለት። ጦቢትም “ከእንግዲህ ወዲህ ምን መልካም ነገር ማግኘት እችላለሁ? ዐይኖቼን አጥቻለሁ፤ የሰማይን ብርሃን ማየት አልችልም፥ ብርሃንን እንደማያዩ ሙታን በጨለማ እገኛለሁ፥ ሕያው ብሆንም ከሞቱት ጋር እቆጠራለሁ፥ ሰዎች ሲናገሩ ድምፃቸውን እሰማለሁ ነገር ግን አላያቸውም” አለ፤ መልአኩም “አይዞህ፥ በቅርቡ እግዚአብሔር ይፈውስሃል፤ አይዞህ” አለው። ጦቢትም “ልጄ ጦብያ ወደ ሜዶን መሄድ ይፈልጋል፤ የመንገድ ጓደኛው በመሆን ልትመራው ትችላለህን? ደሞዝህን እከፍልሃለሁ ወንድሜ።” አለው። እሱም “ከእርሱ ጋር እሄዳለሁ፤ መንገዶቹን ሁሉ አውቃቸዋለሁ፥ ወደ ሜዶን ብዙ ጊዜ ሄጄአለሁ፤ በሜዳዎቹና በተራራዎቹም አቋርጫለሁ፥ መንገዶቹንም ሁሉ አውቃቸዋለሁ” አለው። 11ጦቢትም “ከየትኛው ቤተሰብና ከየትኛው ነገድ ነህ? እስቲ ንገረኝ ወንድሜ” አለው። 12መልአኩም “ነገዴን ማወቅ ምን ይረባሃል?” አለው። ጦቢትም “የማን ልጅ እንደሆንክ እርግጠኛ መሆንና ስምህ ማን መሆኑን ማወቅ እፈልጋለሁ” አለው። 13እርሱም “ስሜ አዛርያ ነው፥ ከዘመዶችህ አንዱ የሆነው የታላቁ አናንያ ልጅ ነኝ” አለው። 14ጦቢትም “ወንድሜ ሆይ እንኳን በደኀና መጣህ፥ ስለ ቤተሰብህ እርግጡን ለማወቅ በመሻቴ አትቀየመኝ፥ ወንድማችን መሆንህ ከጥሩ ዘር መወለድህ አወቅሁ፤ የታላቁ የሸማይያ ሁለት ልጆች አናንያንና ናታንን አውቃቸዋለሁ፤ ከኔ ጋር ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር አብረን እንሰግድ ነበር። ከእምነታቸው ንቅንቅ አላሉም፤ ዘመዶችህ ደጐች ናቸው፥ ከመልካም ዘር ተወልደሃል፤ እንኳን ደኀና መጣህ” አለው። 15ቀጥሎም እንዲህ አለው “ደሞዝህ አንድ ድራክማ በቀን እሰጥሃለሁ፥ በተጨማሪም ለሌላ ወጪህ እኩል ከልጄ ጋር እሰጥሃለሁ፥ ከልጄ ጋር ሂድ፤ 16#ዘፍ. 24፥7፤40።ከደሞዝህ ሌላም እጨምርልሃለሁ።” መልአኩም “ከእርሱ ጋር እሄዳለሁ፥ አትፍራ፤ በደኀና ሄደን በደኀና እንመለሳለን፤ መንገዱ አያሰጋም” አለው። 17ጦቢትም “ተባረክ ወንድሜ” አለው። ልጁንም ጠራና “ልጄ ለመንገድ የሚያስፈልገውን አዘጋጅና ከወንድምህ ጋር ሂዱ፥ በሰማይ ያለ አምላክ በደኀና እዛ ያድርሳችሁ፥ በደኀናና በጤና ወደ እኔ ይመልሳችሁ፥ ልጄ መልአኩ ከእናንተ ጋር ይሂድ፥ ይጠብቃችሁም” አለው። ጦቢያ ከመሄዱ በፊት አባቱንና እናቱን ሳማቸው፤ ጦቢትም “መልካም መንገድ” አለው። 18እናቱ ግን እያለቀሰች ጦቢትን እንዲህ አለችው “ለምንድነው ልጄን የላክኸው? በፊታችን ሲመላለስ የእጃችን ምርኩዝ እሱ አይደለምን? 19ዋናው ጉዳይ ገንዘብ እንዳልሆነ ታውቃለህን? እንደ ልጃችንስ የከበረ ነውን? 20ጌታ የሰጠን ሕይወት ለእኛ በቂያችን ነው።” 21ጦቢትም “እህቴ ሆይ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አታስቢ፥ በደኅና ሄዶ በደኅና ይመለሳል፥ አንቺም በደኅና መመለሱን በዓይንሽ ታያለሽ፥ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አታስቢ፥ ስለ እነርሱም አትጨነቂ፤ 22ደግ መልአክ ከርሱ ጋር ይሄዳል፤ ጉዞውም የተሳካ ይሆናል። በጤንነትና በደስታ ይመለሳል” አላት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጦቢት 5: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ