መጽሐፈ ጦቢት 4
4
4 ጦቢያ
1በዚያኑ ቀን ጦቢት በሜዶን በራጌስ ገባኤል ጋር ያሰቀመጠውን ብር አስታወሰ፥ 2እንዲህ ሲልም አሰበ “እነሆ ልሙት ብዬ ለምኛለሁ፥ ከመሞቴ በፊት ልጄን ጦብያን ጠርቼ ስለ ብሩ ጉዳይ መንገር አለብኝ።” 3ስለዚህ ልጁን ጦቢያን ጠራና እንዲህ አለው፦ “ስሞት በክብር ቅበረኝ፥ እናትህን አክበራት፥ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ አትለያት፥ ደስ የሚላትን ሁሉ አድርግላት፥ በምንም ነገር አታሳዝናት፤ 4ልጄ ሆይ አንተ ገና በማሕፀንዋ ሳለህ ለአንተ ብላ የደረሰባትን መከረ አስታውስ፥ በሞተችም ጊዜ ከጎኔ በአንድ መቃብር ውስጥ ቅበራት። 5ልጄ ሆይ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ለጌታ ታማኝ ሁን፥ ኃጢአትን ለመስራትና ሕጉን ለመተላለፍ አትፍቀድ፥ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ መልካም ሥራን ሥራ፥ መልካም ያልሆኑ መንገዶችን አትከተል፤ 6በእውነተኛነት ከሠራህ በምትሠራው ሥራ ሁሉ ይሳካልሃል፥ ጽድቅን የሚያደርጉ ሁሉ ይቃናላቸዋል፤ 7#ዘዳ. 15፥7፤8፤ ምሳ. 19፥17፤ ሲራ. 3፥30—4፥6፤ 1ዮሐ. 3፥17።ከንብረትህ ሁሉ ምጽዋትን ስጥ፥ ፊትህን በድሆች ላይ አታዙር፥ እግዚአብሔርም ፊቱን ከአንተ አያዞርም። 8ባለህ መጠን ምጽዋት ስጥ፥ ብዙ ካለህ ብዙ ስጥ፥ ጥቂት ካለህም ጥቂት ምጽዋት ለመስጠት አትፍራ፤ 9ይህን በማድረግህ ለክፉ ቀን ትልቅ ሀብት ታከማቻለህ። 10ምጽዋት ከሞት ያተርፋል፥ ወደ ጨለማ ከመግባትም ያድናልና። 11በልዑሉ ፊት ለሚያደርጉት ሁሉ ምጽዋት መስጠት ከሁሉም የላቀ ስጦታ ነው። 12ልጄ ሆይ ከዝሙት ተጠንቀቅ፥ ከሁሉ አስቀድመህ ከአባቶችህ ወገን የሆነች ሴት አግባ፥ እኛ የነቢያት ልጆች ነንና ከአባትህ ነገድ ያልሆነችውን ባዕድ ሴት አታግባ። ልጄ ሆይ ከጥንት ጀምሮ የነበሩትን አባቶቻችንን ኖኀን፥ አብርሃምን፥ ይስሐቅን፥ ያዕቆብን አስብ፤ ሁሉም ሚስት የወሰዱት ከወገኖቻቸው ነው፤ ስለዚህም በልጆቻቸውም የተባረኩ ሆኑ፤ ዘራቸውም ምድርን ይወርሳል። 13አንተም ልጄ ሆይ ወንድሞችህን ውደድ፥ በወንድሞችህ፥ በሕዝብህ ልጆች ላይ አትታበይ፥ ከእነሱ መካከል ሚስት ምረጥ፤ ትዕቢት ጥፋትና ትልቅ ጭንቀት ያመጣልና፥ ስንፍናም ውድቀትንና ድህነትን ያመጣልና፥ የረኃብ እናት ስንፍና ናትና። 14የሰሩልህን ሰዎች ደሞዝ በፍጥነት ከፈል እንጂ ለነገ አታሳድር። እግዚአብሔርን ካገለገልክ ዋጋህን ይከፍልሃል። ልጄ ሆይ በሥራህ ሁሉ ተጠንቀቅ፥ በጠባይህም ሁሉ ሥነ-ሥርዓት ያለህ ሁን። 15#ማቴ. 7፥12፤ ሉቃ. 6፥31።አንተ የማትወደውን ነገር በማንም ላይ አታድርግ፤ እስክትሰክር ድረስ የወይን ጠጅ አትጠጣ፥ ስካር ከአንተ ጋር በመንገድህ አይሂድ። 16ከምግብህ ለተራበ፥ ከልብስህም ለተራቆተ ስጥ፤ የተረፈህን በምጽዋት ስጥ፤ ምጽዋት ስትሰጥ ቅር ሳይልህ ስጥ። 17#ዘዳ. 26፥14።በጻድቅ ቀብር ላይ በምግብና በወይን ለጋስ ሁን፤ ለኃጢአተኛ ግን አይሁን። 18ከእያንዳንዱ ጠቢብ ሰው ምክርን ፈልግ፥ የሚጠቅም ምክርን አትናቅ። 19ሁልጊዜ ጌታ እግዚአብሔርን አመስግን፤ መንገድህን ሁሉ እንዲያቃናልህ ጎዳናህንና ትልምህን ወደ ፍጻሜ እንዲያደርሰው ለምነው። ጥበብ የሁሉም ሕዝብ ሀብት አይደለምና፤ ነገር ግን መልካም ነገሮችን ጌታ ይሰጣል፤ እንደ ፈቃዱ ከፍ ያደርጋል ወይም ሙታን ወደሚኖሩበት ጥልቅ ይጥላል፥ አሁንም ልጄ ሆይ እነዚህን ምክሮች አስታውሳቸው፥ ከልብህም አይጥፉ። 20አሁንም ልጄ ሆይ በሜዶን አገር በራጌስ በገብርያስ ልጅ በገባኤል ዘንድ አስር ታለንት ብር ማስቀመጤን ልነግርህ እወዳለሁ። 21#1ጢሞ. 6፥6-8።ልጄ ሆይ ድሆች በመሆናችን አትፍራ፤ እግዚአብሔርን ከፈራህና ከኃጢአት ሁሉ ከራቅክ፥ ጌታ አምላክህን ደስ የሚያሰኘው ነገር ሁሉ ካደረግህ ብዙ ሀብት አለህ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ጦቢት 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ