መጽ​ሐፈ ጦቢት 8

8
መቃብሩ
1ከበሉና ከጠጡ በኋላ ወደ መኝታ ቤታቸው ለመሄድ ተነሡ፤ ወጣቱንም ወሰዱትና ወደ ተዘጋጀው መኝታ ቤት አስገቡት። 2ጦብያ ሩፋኤል የነገረውን አስታወሰ፤ ከከረጢቱ የዓሣውን ጉበትና ልብ አውጥቶ በዕጣን ማጨሻው ላይ አደረገው። 3#ማቴ. 12፥43።የዓሣው ሽታ ጋኔኑን አሸሸው፤ ጋኔኑ በአየር ላይ ወደ ግብጽ አገር ሸሸ፤ ሩፋኤል ወዲያውኑ ተከታትሎ ያዘውና እጅና አግሩን አሰረው። 4የሣራ ወላጆች ወጡና በሩን ከኋላቸው ዘጉት፤ በዚያን ጊዜ ጦብያ ከአልጋው ተነሣና ሣራን “እኀቴ ተነሽ ጌታችን ጸጋውንና ጥበቃውን እንዲያበዛልብ መጸለይና መለመን አለብን” አላት። 5እርሷም ተነሣች፤ እንዲጠብቃቸው መጸለይና መለመን ጀመሩ፥ እንዲህም ሲል መጸለይ ጀመረ “የአባቶቻችን አምላክ ሆይ ብሩክ ነህ፤ ስምህም ለዘለዓለም ዓለም የተባረከ ነው፤ ሰማያትና የፈጠርካቸው ሁሉ ለዘለዓለም ይባርኩህ፤ 6#ዘፍ. 2፥18።አዳምን የፈጠርህ አንተ ነህ፥ ረዳትና አጋዥ እንድትሆነው ሚስቱን ሔዋንን የፈጠርህለት አንተ ነህ፤ የሰው ዘር ሁሉ የተወለደው ከሁለቱ ነው። ‘ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም፥ እሱን የምትመስል ረዳት እንፈጠርለት’ ያልህ አንተ ነህ። 7አሁንም ይህችን እኀቴን የማገባት በዝሙት መንፈስ ተይዤ ሣይሆን በእውነተኛነት ነው፤ በእኔም በእርሷም ላይ ምሕረትህን አውርድልን፤ አብረንም ለሽምግልና አብቃን። 8ሁለቱም አብረው ‘አሜን አሜን’ አሉ። 9ከዚህ በኋላ አብረው አደሩ። ራጉኤል ግን ተነሣና አገልጋዮቹን ጠራ፤ ከእርሱ ጋር ሄዱና የመቃብር ቦታ ቆፈሩ፤ 10‘እሱም ይሞታል እኛም የሰዎች መሳቂያና ማላገጫ እንሆናለን’ ብሎ አስቧልና።” 11መቃብሩን ቆፍረው ከጨረሱ በኋላ ራጉኤል ወደ ቤቱ ሄዳና ሚስቱን ጠራት፤ 12እንዲህም አላት፦ “ጦብያ በሕይወት እንዳለ ለማየት ከአገልጋዮቹ አንዲቱን ወደ መኝታ ቤቱ ላኪ፤ ሞቶ ከሆነ ማንም ሰው ሳያውቅ እንድንቀብረው።” 13ከዚያም አገልጋይቱን ላኳት፥ እስዋም ፋኖሱን አብርታ በሩን ከፍታ ወደ ውስጥ ገባች፥ ሁለቱም ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዷቸው አገኘቻቸው፤ 14ወጣችና “እሱ አልሞተም ሁሉም ነገር ሰላም ነው።” አለቻቸው። 15ከዚህ በኋላ ራጉኤል የሰማዩን አምለክ በእነዚህ ቃላት እንዲህ ሲል ባረከ “አምላኬ ሆይ ንጹሕ በሆነ በረከት አንተ ብሩክ ነህ፤ ለዘለዓለሙ ብሩክ ሁን። 16ደስ ስላሰኘኸኝ አንተ ብሩክ ነህ፤ ወሰን የሌለውን ምሕረትህን አሳየኸን እንጂ የፈራሁት አልደረሰም። 17ለወላጆቻቸው አንድ የሆኑትን ልጆች ስለራራህላቸው አንተ ብሩክ ነህ። አሁንም ጌታ ሆይ ምሕረትህንና ጥበቃህን ስጣቸው፤ ሕይወታቸውን በደስታና በምሕረት እንዲመሩ አድርጋቸው።” 18ከዚህ በኋላ አገልጋዮቹን ሳይነጋ መቃብሩን እንዲደፍኑት አዘዛቸው። 19ሚስቱ ዳቦ በብዛት እንድትጋግር ነገራት፤ ወደ ከብቶቹ መንጋ ሄደና ሁለት ሰንጋዎችና አራት ሙክቶች አምጥቶ ታርደው እንዲዘጋጁ አዘዘ፥ ዝግጅቱም ተጀመረ። 20#ዘፍ. 24፥55።እስሱም ጦብያን ጠርቶ “እንግዲህ ወዴትም ሳትሄዱ እዚህ እየበላህና እየጠጣህ ዐሥራ አራት ቀን ከእኔ ጋር ትቆያለህ፥ ብዙ መከራ የደረሰባትን ልጄንም ታስደስታታለህ። 21ከዛ በኋላ የንብረቴን ግማሹን ውሰድና ያለ ምንም ችግር ይዘሃት ወደ አባትህ ቤት ሂድ፤ የቀረውን ግማሽ ደግሞ እኔና ሚስቴ ስንሞት የእናንተ ይሆናል፤ በርታ ልጄ፥ እኔ አባትህ ነኝ፥ ኤድናም እናትህ ናት፥ ከእኀትህ ወላጆች እንደ ሆንን የአንተም ነን፥ በርታ ልጄ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ