መዝሙረ ዳዊት 94:12-23

መዝሙረ ዳዊት 94:12-23 መቅካእኤ

ለክፉ ሰው ጉድጓድ እስኪቈፈር ድረስ ከአስከፊ ዘመናት ይወገድ ዘንድ፥ አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ብፁዕ ነው። ጌታ ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና ፍርድ ወደ ጽድቅ እስክትመለስ ድረስ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይከተሉአታል። በክፉዎች ላይ ለእኔ የሚነሣ ማን ነው? ዓመፅንስ በሚያደርጉ ላይ ለእኔ የሚከራከር ማን ነው? ጌታ ባይረዳኝ ኖሮ ነፍሴ ወዲያው ሲኦል በወረደች ነበር። እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ጽኑ ፍቅርህ ረዳኝ። አቤቱ፥ የልቤ መረበሽ በበዛ መጠን፥ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት። በሕግ ስም ዓመፅን የሚሠራ የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋር አንድ ይሆናልን? የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፥ በንጹሕ ደም ላይም ይፈርዳሉ። ጌታ መጠጊያ ሆነኝ፥ አምላኬ የመጠለያዬ ዓለት ነው። እንደ በደላቸውም፥ እንደ ክፋታቸውም ፍዳቸውን ይከፍላቸዋል፥ ጌታ አምላካችን ያጠፋቸዋል።