መዝሙር 94:12-23

መዝሙር 94:12-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የምትገሥጸው፣ ከሕግህም የምታስተምረው ሰው፤ ለኀጢአተኞች ጕድጓድ እስኪማስላቸው ድረስ፣ እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ። እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፤ ርስቱንም አይተውም። ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል፤ ልባቸውም ቀና የሆነ ሁሉ ይከተሉታል። ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው? ከክፉ አድራጊዎችስ ጋራ የሚሟገትልኝ ማን ነው? እግዚአብሔር ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣ ነፍሴ ወደ ዝምታው ዓለም ፈጥና በወረደች ነበር። እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ። የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት። ዐመፃን ሕጋዊ የሚያደርግ፣ የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋራ ሊያብር ይችላልን? በጻድቁ ላይ ተሰልፈው ይወጣሉ፤ በንጹሑም ላይ ሞት ይፈርዳሉ። ለእኔ ግን እግዚአብሔር ምሽግ፣ አምላኬም መጠጊያ ዐለት ሆኖኛል። በደላቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፤ በክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ይደመስሳቸዋል።

መዝሙር 94:12-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የምትገሥጸውና ሕግህንም የምታስተምረው ሰው እንዴት የተባረከ ነው! ለክፉዎች ጒድጓድ እስኪቈፈር ድረስ እርሱን በመከራ ቀኖች ታሳርፈዋለህ። እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም፤ የእርሱ የሆኑትንም አይተዋቸውም። ፍትሕ እንደገና የዳኝነት መሠረት ትሆናለች፤ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይደግፉአታል። ዐመፀኞችን ለመቃወም ከጐኔ የሚቆም ማነው? ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር ስለ እኔ የሚከራከር ማን ነው? እግዚአብሔር ባይረዳኝ ኖሮ፥ ፈጥኜ ወደ ሙታን ዓለም በወረድኩ ነበር። “ለመውደቅ ተቃርቤአለሁ” ባልኩ ጊዜ እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ደግፎ አቆመኝ። አስጨናቂ ሐሳብ ልቤን በሞላው ጊዜ ማጽናናትህ ደስታን ሰጠኝ። በሕግ ሽፋን በተቀነባበረ ተንኰል ለተዛባ ፍትሕ ተባባሪ ትሆናለህን? እነርሱ በደጋግ ሰዎች ላይ ያሤራሉ፤ በንጹሓን ሰዎች ላይም የሞት ፍርድ ይበይናሉ። ለእኔ ግን እግዚአብሔር መከታዬ ነው፤ አምላኬ መጠጊያዬ ነው። እርሱ ስለ ክፋታቸው ይቀጣቸዋል፤ ስለ ኃጢአታቸውም ይደመስሳቸዋል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ያጠፋቸዋል።