መጽሐፈ መዝሙር 94:12-23

መጽሐፈ መዝሙር 94:12-23 አማ05

እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የምትገሥጸውና ሕግህንም የምታስተምረው ሰው እንዴት የተባረከ ነው! ለክፉዎች ጒድጓድ እስኪቈፈር ድረስ እርሱን በመከራ ቀኖች ታሳርፈዋለህ። እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም፤ የእርሱ የሆኑትንም አይተዋቸውም። ፍትሕ እንደገና የዳኝነት መሠረት ትሆናለች፤ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይደግፉአታል። ዐመፀኞችን ለመቃወም ከጐኔ የሚቆም ማነው? ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር ስለ እኔ የሚከራከር ማን ነው? እግዚአብሔር ባይረዳኝ ኖሮ፥ ፈጥኜ ወደ ሙታን ዓለም በወረድኩ ነበር። “ለመውደቅ ተቃርቤአለሁ” ባልኩ ጊዜ እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ደግፎ አቆመኝ። አስጨናቂ ሐሳብ ልቤን በሞላው ጊዜ ማጽናናትህ ደስታን ሰጠኝ። በሕግ ሽፋን በተቀነባበረ ተንኰል ለተዛባ ፍትሕ ተባባሪ ትሆናለህን? እነርሱ በደጋግ ሰዎች ላይ ያሤራሉ፤ በንጹሓን ሰዎች ላይም የሞት ፍርድ ይበይናሉ። ለእኔ ግን እግዚአብሔር መከታዬ ነው፤ አምላኬ መጠጊያዬ ነው። እርሱ ስለ ክፋታቸው ይቀጣቸዋል፤ ስለ ኃጢአታቸውም ይደመስሳቸዋል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ያጠፋቸዋል።