መዝሙረ ዳዊት 18:1-29

መዝሙረ ዳዊት 18:1-29 መቅካእኤ

አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። ጌታ ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ዓለቴ፥ ጋሻዬ፥ የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ገመዶች ጠፍረው ያዙኝ፥ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ፥ የሲኦል ገመዶች ተበተቡኝ፥ የሞት ወጥመዶችም ደረሱብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፥ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ ተናጉም እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና። ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፥ ፍምም ከእርሱ በራ። ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩቤልም ሠረገላ ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ አንዣበበ። መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፥ በዙሪያውም ድንኳኑ፥ በውሃ የተሞሉ ጥቁር ደመናዎች ሸፍነውታል። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ። ጌታ ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። በረዶና የእሳት ፍምም፤ ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፥ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም። አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከአፍንጫህ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፥ ጌታ ግን ድጋፍ ሆነኝ። ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፥ ወድዶኛልና አዳነኝ። ጌታ እንደጽድቄ ይከፍለኛል፥ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል። የጌታን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም። በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። ጌታም እንደጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዐይኖቹ ፊት መለሰልኝ። ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፥ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከጠማማም ጋር ብልህ ሆነህ ትገኛለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዐይን ግን ታዋርዳለህ። አንተ መብራቴን ታበራለህና፥ ጊታ አምላኬ ጨለማዬን ያበራል።