መዝሙር 18:1-29

መዝሙር 18:1-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጕልበቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ እወድድሃለሁ። እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ፤ እርሱ ጋሻዬ፣ የድነቴ ቀንድና ዐምባዬ ነው። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ገመድ ዐነቀኝ፤ ምናምንቴ ነገርም አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጋረጠብኝ። በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም በፊቱ ከጆሮው ደረሰ። ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤ የተራሮችም መሠረቶች ተናጉ፤ እርሱ ተቈጥቷልና ተንቀጠቀጡ። ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፤ ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤ ከውስጡም ፍሙ ጋለ። ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ። በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ መጠቀ። ጨለማን መሰወሪያው፣ በዙሪያውም አጐበሩ አደረገው፤ በዝናብ ዐዘል ጥቍር ደመናም ተሸፈነ። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ፣ ደመናት፣ የበረዶ ድንጋይና መብረቅ ወጡ። እግዚአብሔር ከሰማያት አንጐደጐደ፤ የልዑልም ድምፅ አስተጋባ። ፍላጻውን ሰድዶ በተናቸው፤ ታላቅ መብረቆቹንም ልኮ አወካቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተግሣጽህ የተነሣ፣ ከአፍንጫህም እስትንፋስ የተነሣ፣ የባሕር ወለል ታየ፤ የምድር መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ፤ ከብርቱ ጠላቶቼ አዳነኝ፤ ከሚበረቱብኝ ባላጋሮቼም ታደገኝ። እነርሱ በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ። ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም። ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም። በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤ ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን፣ በፊቱ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ። ለታማኝ ሰው ታማኝ መሆንህን፣ ለፍጹም ሰው ፍጹም መሆንህን ታሳያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣ ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ። አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤ ትዕቢተኛውን ዐይን ግን ታዋርዳለህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴን ታበራለህ፤ አምላኬ፤ ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ጕልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ።

መዝሙር 18:1-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሆይ! ኀይል የምትሰጠኝ አንተ ስለ ሆንክ፥ እወድሃለሁ። እግዚአብሔር አለቴ፥ አምባዬና አዳኜ ነው፤ አምላኬ የምጠጋበት አለቴ ነው፤ እርሱ ጋሻዬና የመዳኔ ቀን፥ ጠንካራ መመኪያም ነው። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ እርሱም ከጠላቶቼ ያድነኛል። የሞት ጣር ከበበኝ፤ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ። መከራ በደረሰብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም አምላኬን ለመንኩት፤ በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴንም አደመጠ። እግዚአብሔር ስለ ተቈጣ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤ የተራሮች መሠረቶች ተናጉ፤ ተነቃነቁም። ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤ ከአፉም የሚባላ የእሳት ነበልባልና የሚያቃጥል ፍም ወጣ። ሰማይን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ። በኪሩቤል ላይ ሆኖ በረረ፤ በነፋስ ክንፎች ላይ ሆኖ ወደ ላይ መጠቀ። ሁለንተናውን በጨለማ ሸፈነ፤ በውሃ የተሞላ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከቦታል። በፊቱ ካለው ነጸብራቅ በረዶና የእሳት ብልጭታ ጥቅጥቅ ያለውን ደመና ሰንጥቆ ወጣ። እግዚአብሔር ከሰማይ አንጐደጐደ፤ ልዑል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማ። ፍላጻውን ከቀስቱ አስፈነጠረ፤ ጠላቶቹንም በተናቸው፤ በመብረቁም ብልጭታ አሳደዳቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህን በገሠጽህ ጊዜ፥ የቊጣ ድምፅህንም ባሰማህ ጊዜ የውቅያኖስ ወለል ታየ፤ የምድርም መሠረት ተጋለጠ። እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ እጁን በመዘርጋት ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሃም ስቦ አወጣኝ። በጣም በርትተውብኝ ከነበሩት ከኀይለኞች ጠላቶቼና ከሚጠሉኝ ሰዎች ሁሉ እጅ እግዚአብሔር አዳነኝ። እኔ በተቸገርኩበት ጊዜ በጠላትነት ተነሡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ጠበቀኝ። ወደ ሰፊ ቦታ አወጣኝ፤ በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄም ንጽሕና ይመልስልኛል። እኔ የእግዚአብሔርን መንገድ ተከትዬአለሁ፤ ፊቴን ከአምላኬ በመመለስ ክፉ ነገር አላደረግሁም። የእግዚአብሔርን ሕጎች ሁሉ እፈጽማለሁ ሥርዓቱንም ከማክበር ወደ ኋላ አላልኩም። በእርሱ ዘንድ ንጹሕ ነበርኩ፤ ከኃጢአትም ራሴን ጠብቄአለሁ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና፥ ዋጋዬን ከፈለኝ። አምላክ ሆይ! ለአንተ ታማኞች ለሆኑት ታማኝ ነህ፤ እውነተኞች ለሆኑትም እውነተኛ ነህ። ለንጹሖች ንጹሕ ነህ፤ ለጠማሞች ግን ተገቢ ዋጋቸውን ትሰጣለህ። ትሑቶችን ታድናለህ፤ ትዕቢተኞችን ግን ታዋርዳለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ለእኔ ብርሃኔ ነህ፤ አንተ አምላኬ ጨለማዬን ታበራለህ። በአንተ ርዳታ አንድ የጦር ጓድ አጠቃለሁ፤ አንተ አምላኬም ቅጥሩን ለመዝለል ትረዳኛለህ።

መዝሙር 18:1-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ ጉልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። ጌታ ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ዓለቴ፥ ጋሻዬ፥ የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው። ምስጋና የሚገባውን ጌታን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ገመዶች ጠፍረው ያዙኝ፥ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ፥ የሲኦል ገመዶች ተበተቡኝ፥ የሞት ወጥመዶችም ደረሱብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፥ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ ተናጉም እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና። ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፥ ፍምም ከእርሱ በራ። ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩቤልም ሠረገላ ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ አንዣበበ። መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፥ በዙሪያውም ድንኳኑ፥ በውሃ የተሞሉ ጥቁር ደመናዎች ሸፍነውታል። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ። ጌታ ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። በረዶና የእሳት ፍምም፤ ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፥ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም። አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከአፍንጫህ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፥ ጌታ ግን ድጋፍ ሆነኝ። ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፥ ወድዶኛልና አዳነኝ። ጌታ እንደጽድቄ ይከፍለኛል፥ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል። የጌታን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም። በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። ጌታም እንደጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዐይኖቹ ፊት መለሰልኝ። ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፥ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከጠማማም ጋር ብልህ ሆነህ ትገኛለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዐይን ግን ታዋርዳለህ። አንተ መብራቴን ታበራለህና፥ ጊታ አምላኬ ጨለማዬን ያበራል።

መዝሙር 18:1-29

መዝሙር 18:1-29 NASV