እግዚአብሔር ሆይ! ኀይል የምትሰጠኝ አንተ ስለ ሆንክ፥ እወድሃለሁ። እግዚአብሔር አለቴ፥ አምባዬና አዳኜ ነው፤ አምላኬ የምጠጋበት አለቴ ነው፤ እርሱ ጋሻዬና የመዳኔ ቀን፥ ጠንካራ መመኪያም ነው። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ እርሱም ከጠላቶቼ ያድነኛል። የሞት ጣር ከበበኝ፤ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ። መከራ በደረሰብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም አምላኬን ለመንኩት፤ በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴንም አደመጠ። እግዚአብሔር ስለ ተቈጣ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤ የተራሮች መሠረቶች ተናጉ፤ ተነቃነቁም። ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤ ከአፉም የሚባላ የእሳት ነበልባልና የሚያቃጥል ፍም ወጣ። ሰማይን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ። በኪሩቤል ላይ ሆኖ በረረ፤ በነፋስ ክንፎች ላይ ሆኖ ወደ ላይ መጠቀ። ሁለንተናውን በጨለማ ሸፈነ፤ በውሃ የተሞላ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከቦታል። በፊቱ ካለው ነጸብራቅ በረዶና የእሳት ብልጭታ ጥቅጥቅ ያለውን ደመና ሰንጥቆ ወጣ። እግዚአብሔር ከሰማይ አንጐደጐደ፤ ልዑል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማ። ፍላጻውን ከቀስቱ አስፈነጠረ፤ ጠላቶቹንም በተናቸው፤ በመብረቁም ብልጭታ አሳደዳቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህን በገሠጽህ ጊዜ፥ የቊጣ ድምፅህንም ባሰማህ ጊዜ የውቅያኖስ ወለል ታየ፤ የምድርም መሠረት ተጋለጠ። እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ እጁን በመዘርጋት ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሃም ስቦ አወጣኝ። በጣም በርትተውብኝ ከነበሩት ከኀይለኞች ጠላቶቼና ከሚጠሉኝ ሰዎች ሁሉ እጅ እግዚአብሔር አዳነኝ። እኔ በተቸገርኩበት ጊዜ በጠላትነት ተነሡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ጠበቀኝ። ወደ ሰፊ ቦታ አወጣኝ፤ በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄም ንጽሕና ይመልስልኛል። እኔ የእግዚአብሔርን መንገድ ተከትዬአለሁ፤ ፊቴን ከአምላኬ በመመለስ ክፉ ነገር አላደረግሁም። የእግዚአብሔርን ሕጎች ሁሉ እፈጽማለሁ ሥርዓቱንም ከማክበር ወደ ኋላ አላልኩም። በእርሱ ዘንድ ንጹሕ ነበርኩ፤ ከኃጢአትም ራሴን ጠብቄአለሁ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና፥ ዋጋዬን ከፈለኝ። አምላክ ሆይ! ለአንተ ታማኞች ለሆኑት ታማኝ ነህ፤ እውነተኞች ለሆኑትም እውነተኛ ነህ። ለንጹሖች ንጹሕ ነህ፤ ለጠማሞች ግን ተገቢ ዋጋቸውን ትሰጣለህ። ትሑቶችን ታድናለህ፤ ትዕቢተኞችን ግን ታዋርዳለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ለእኔ ብርሃኔ ነህ፤ አንተ አምላኬ ጨለማዬን ታበራለህ። በአንተ ርዳታ አንድ የጦር ጓድ አጠቃለሁ፤ አንተ አምላኬም ቅጥሩን ለመዝለል ትረዳኛለህ።
መጽሐፈ መዝሙር 18 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 18:1-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች