መጽሐፈ ምሳሌ 31
31
1እናቱ ያስተማረችው የማሣ ንጉሥ፥ የልሙኤል ቃል።
2ልጄ ሆይ፥ ምንድነው? የሆዴ ልጅ ሆይ፥ ምንድነው?
የስእለቴ ልጅ ሆይ፥ ምንድነው?
3ጉልበትህን ለሴቶች አትስጥ፥
መንገድህንም ነገሥታትን ለሚያጠፉ።
4ለነገሥታት አይገባም፥ ልሙኤል ሆይ፥ ነገሥታት የወይን ጠጅ ሊጠጡ፥
መሳፍንትም፦ ብርቱ መጠጥ ወዴት ነው? ሊሉ አይገባም፥
5ጠጥተው ሕግን እንዳይረሱ፥
የድሀ ልጆችንም ፍርድ እንዳያጐድሉ።
6ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥
ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፥
7ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥
ጉስቁልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ።
8ስለ ዲዳው ተናገር፥
ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ።
9ተናገር፥ በእውነትም ፍረድ፥
ለድሀና ለምስኪን ፍረድ።
10ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል?
ዋጋዋ ከቀይ ዕንቁ እጅግ ይበልጣል።
11የባሏ ልብ ይታመንባታል።
መልካም ነገር አይጐድልበትም።
12ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥
ክፉም አታደርግም።
13የበግ ጠጉርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥
በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች።
14እርሷ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፥
ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች።
15ገና ሳይነጋ ትነሣለች
ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥
ለአገልጋዮችዋም ሥራ ትሰጣለች።
16እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፥
ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች።
17ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥
ክንድዋንም ታበረታለች።
18ማትረፍዋን ታስተውላለች፥
መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም።
19እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥
ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ።
20እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥
ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች።
21ለቤትዋ ሰዎች ብርድን#31፥21 በበረዶ ወቅት ያለውን ብርድ። አትፈራም፥
የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ#31፥21 ወይም የሚያሞቅ ውድ ልብስ። የለበሱ ናቸውና።
22ለራስዋም የአልጋ ልብስ ትሠራለች
ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች።
23ባሏ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ
በበር#31፥23 የከተማ በር። የታወቀ ይሆናል።
24የበፍታ ልብስ እየሠራች ትሸጣለች፥
ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች።
25ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፥
በሚመጣውም ዘመን ላይ ትስቃለች።
26በጥበብ ትናገራለች፥
የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ።
27የቤትዋንም ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፥
የሀኬትንም እንጀራ አትበላም።
28ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጉን ነሽ ይሏታል፥
ባሏ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል፦
29“መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥
አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።”
30ደም ግባት ሐሰት ነው፥ ውበትም ከንቱ ነው፥
ጌታን የምትፈራ ሴት ግን እርሷ ትመሰገናለች።
31ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፥
ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 31: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ