መጽሐፈ ምሳሌ 30

30
1የማሣ አገር ሰው የያቄ ልጅ የአጉር ቃል።
ሰውየው ለኢቲኤልና ለኡካል እንደዚህ ይናገራል፦
2እኔ በእውነት ከሰው ሁሉ ይልቅ ደንቆሮ ነኝ፥
የሰውም ማስተዋል የለብኝም።
3ጥበብንም አልተማርሁም፥
ቅዱሱንም አላወቅሁትም።
4ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው?
ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው?
ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው?
የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው?
ይህን ታውቅ እንደሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?
5የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ የጠራ ነው፥
እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው።
6እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን
በቃሉ አንዳች አትጨምር።
7ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥
ሳልሞትም አትከልክለኝ፥
8ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፥
ድህነትንና ሀብታምነትን አትስጠኝ፥
የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥
9እንዳልጠግብ እንዳልክድህም፦
“ጌታስ ማን ነው?” እንዳልል፥
ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥
የአምላኬንም ስም እንዳላረክስ።
10እንዳይሰድብህ በደለኛም እንዳትሆን
ባርያን በጌታው ፊት በሐሰት አትተች።
11አባቱን የሚረግም፥
እናቱንም የማያመሰግን ትውልድ አለ።
12ለራሱ ንጹሕ የሆነ የሚመስለው
ከርኩሰቱ ግን ያልጠራ ትውልድ አለ።
13በትዕቢት ከፍ ከፍ ያሉ ዐይኖች ያሉት፥
ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ።
14ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ለማጥፋትና ለመጨረስ
ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ።
15አልቅት#30፥15 ትዕቢተኛ። “ስጠን ስጠን” የሚሉ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉት።
ሦስቱ የማይጠግቡ አራቱም፦ “በቃን” የማይሉ ናቸው፥
16እነርሱም ሲኦልና የማትወልድ ማኅፀን፥
ውኃ የማትጠግብ ምድርና፦
“በቃኝ” የማትል እሳት ናቸው።
17በአባትዋ የምታላግጥን
የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዐይን
የሸለቆ ቁራዎች ይጐጠጉጡአታል፥
አሞራዎችም ይበሉአታል።
18ሦስት ነገር ይገርመኛል፥
አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም።
19 # ጥበ. 5፥10-12። እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥
የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥
የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥
የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ናቸው። 20የአመንዝራ ሴት መንገድም እንዲሁ ነው።
በልታ አፍዋን የምታብስ፦
“አንዳች ክፉ ነገርም አላደረግሁም” የምትል።
21በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥
አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም።
22አገልጋይ በነገሠ ጊዜ፥#30፥22 ከታች ወደ ላይ በሥልጣን መውጣት።
ሞኝ እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥
23የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥
ሴት አገልጋይም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ።
24በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፥
እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፥
25ገብረ ጉንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥
ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ።
26ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥
ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ።
27አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፥
ሁላቸውም ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ።
28እንሽላሊት በእጅ ይያዛል፥
በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል።
29መልካም አረማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥
አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፥
30የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥
ማንንም ፈርቶ የማይመለስ፥
31በእንስቶች መካከል በድፍረት የሚራመድ አውራ ዶሮ፥
መንጋን የሚመራ አውራ ፍየል፥
በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚናገር ንጉሥ።
32ከፍ ከፍ በማለት የተሞኝህ እንደሆነ፥
ክፉም ያሰብህ እንደሆነ፥
እጅህን በአፍህ ላይ ጫን።
33ወተት መናጥ ቅቤን ያወጣል፥
አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣል፥
እንዲሁም ቁጣን መጐተት ጠብን ያመጣል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ