የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 13

13
የእስራኤላውያን ከባዕዳን ሕዝቦች መለየት
1 # ዘዳ. 23፥3-6። በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ ከፍ ባለ ድምፅ አነበቡ፤ አሞናዊ ወይም ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘለዓለም እንዳይገባ የሚል በዚያ ተጽፎ ተገኘ። 2#ዘኍ. 22—24።ይህም ደግሞ የእስራኤልን ልጆች በምግብና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና እንዲረግማቸውም በለዓምን ስለ ገዙት ነው፤ ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው። 3#ነህ. 13፥23-28።እንዲህም ሆነ ሕጉን በሰሙ ጊዜ የተደባለቀውን ዘር ሁሉ ከእስራኤል ለዩ።
ነህምያ ያደረጋቸው ለውጦች
4ከዚህ ቀደም በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሾሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሺብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ፥ 5#ነህ. 12፥44።ትልቅ ለሌዋውያን፥ ለመዘምራን፥ ለበረኞቹ እንደ ሕጉ የተሰጣቸውን የእህሉን ቁርባንና ዕጣኑን፥ ዕቃዎቹንም፥ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት፥ ለካህናቱም የሆነውን የማንሣት ቁርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር። 6በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም፤ በባቢሎን ንጉሥ በአርታሕሻስት በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበርና፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከንጉሡ ፈቃድ ጠየቅሁ፤ 7ወደ ኢየሩሳሌምም መጣሁ፥ ኤልያሺብ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ። 8እጅግም አስከፋኝ፥ የጦብያንም የቤቱን ዕቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጪ ጣልሁ። 9ጓዳዎቹንም እንዲያነጹ አዘዝሁ፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃዎች የእህሉንም ቁርባን ዕጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ።
10 # ዘዳ. 12፥19። ለሌዋውያንም እድል ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፥ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደ ሄዱ ተመለከትሁ። 11እኔም፦ የእግዚአብሔር ቤት ስለምን ተተወ? ብዬ ከአለቆቹ ጋር ተከራከርሁ። ሰበሰብኋቸውም፥ በየስፍራቸውም አቆምኋቸው። 12#ነህ. 10፥38-39፤ 12፥44-45፤47፤ 2ዜ.መ. 31፥6።ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ። 13በዕቃ ቤቶችም ላይ ካህኑን ሰሌምያን፥ ጸሐፊውንም ሳዶቅን፥ ከሌዋውያኑም ፈዳያን ሾምሁ፥ ከእነርሱም ጋር የማታንያ ልጅ የዘኩር ልጅ ሐናን ነበረ፥ እነርሱም የታመኑ ሆነው ተገኙ፥ ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው ማከፋፈል ነበረ። 14አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ፥ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ።
15 # ነህ. 10፥32፤ ዘፀ. 20፥8። በዚያም ወራት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጥመቂያን የሚረግጡትን፥ ነዶም የሚከመሩትን፥ የወይኑን ጠጅና የወይኑን ዘለላ በለሱንም ልዩ ልዩም ዓይነት ሸክም በአህዮች ላይ የሚጭኑትን፥ በሰንበትም ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያስገቡትን አየሁ፥ ገበያ ባደረጉበትም ቀን አስመሰከርሁባቸው። 16ደግሞም በእርሷ የተቀመጡ የጢሮስ ሰዎች ነበሩ፥ እነርሱም ዓሣዎችን ልዩ ልዩም ዓይነት ሸቀጥ አምጥተው በሰንበት ቀን በኢየሩሳሌም ለይሁዳ ልጆች ይሸጡ ነበር። 17ከይሁዳም ታላላቆች ጋር ተከራከርሁና፦ ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድነው? የሰንበትንስ ቀን ታረክሳላችሁን? 18አባቶቻችሁ እንደዚህ አድርገው አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ በእኛና በዚህ ከተማ ላይ አምጥቶ አልነበረምን? እናንተም ሰንበትን በማርከሳችሁ በእስራኤል ላይ መዓትን ትጨምራላችሁ አልኋቸው።
19ከዚህ በኋላ ከሰንበት በፊት በኢየሩሳሌም በሮች ድንግዝግዝታ በሆነ ጊዜ በሮችዋ እንዲዘጉ፥ ሰንበትም እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ። በሰንበትም ቀን ሸክም እንዳይገባ ከብላቴኖቼ በአያሌዎቹ በሮችዋን አስጠበቅሁ። 20ሁሉም አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በኢየሩሳሌም ውጭ አድረው ገበያ አድርገው ነበር። 21እኔም አስመሰከርሁባቸውና፦ በቅጥሩ ውጭ ለምን ታድራላችሁ? እንደገና ብታደርጉት እጆቼን አነሣባችኋለሁ አልኋቸው። ከዚያም ወዲያ በሰንበት ቀን እንደገና አልመጡም። 22ሌዋውያኑንም ራሳቸውን እንዲያነጹ፥ መጥተውም በሮቹን እንዲጠብቁ፥ የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ ነገርኋቸው። አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ራራልኝ።
23 # ነህ. 10፥31፤ 13፥1-3፤ ዘዳ. 23፥3፤ ዕዝ. 9—10። ደግሞም በዚያ ወራት የአዛጦንና የአሞንን የሞዓብንም ሴቶች ያገቡትን አይሁድ አየሁ። 24ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ በአዛጦን ቋንቋ ይናገሩ ነበር፥ በአይሁድም ቋንቋ መናገር አያውቁም ነበር። 25ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ፥ ረገምኋቸውም፥ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታሁ፥ ጠጉራቸውንም ነጨሁ፥ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው፦ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተና ለልጆቻችሁ አትውሰዱ። 26#1ነገ. 11፥1-13።የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በዚህ ነገር ኃጢአት አድርጎ የለምን? በብዙ አሕዛብም መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፥ በአምላኩም ዘንድ የተወደደ ነበረ፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ አንግሦት ነበር፥ እርሱንም እንኳ እንግዶች ሴቶች አሳቱት። 27በውኑ ይህን ሁሉ ታላቅ ክፋት እንሠራ፥ እንግዶችንም ሴቶች በማግባት አምላካችንን እንበድል ዘንድ እናንተን እንስማ?
28 # ነህ. 2፥10፤ 13፥4-5፤7-9። ከዋነኛውም ካህን ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ ለሖሮናዊው ለሰንበላጥ አማች ነበረ፥ ከእኔም ዘንድ አባረርሁት። 29አምላኬ ሆይ፥ ክህነትን የክህነትንና የሌዋውያንንም ቃል ኪዳን ስላፈረሱ አስባቸው።
30ከእንግዳ ነገርም ሁሉ አነጻኋቸው፥ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው በየሰሞናቸው፥ 31#ነህ. 10፥35-36።በየጊዜውም ለእንጨት ቁርባን ለበኩራቱም ሥርዓት አደረግሁ። አምላኬ ሆይ፥ በመልካም አስበኝ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ