የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 12

12
የካህናትና የሌዋውያን ስም ዝርዝር
1 # ነህ. 12፥12-22። ከሰላትያል ልጅ ከዘሩባቤልና ከኢያሱ ጋር የወጡት ካህናትና ሌዋውያን እነዚህ ናቸው፤ ሥራያ፥ ኤርምያስ፥ ዕዝራ፥ 2አማርያ፥ ማሉክ፥ ሐጡሽ፥ 3ሽካንያ፥ ርሁም፥ ምሬሞት፥ 4ዒዶ፥ ጊንቶይ፥ አቢያ፥ 5ሚያሚን፥ ማዓድያ፥ ቢልጋ፥ 6ሽማዕያ፥ ዮያሪብ፥ ይዳዕያ፥ 7ሳሉ፥ ዓሞቅ፥ ሒልቂያ፥ ይዳዕያ፤ እነዚህ በኢያሱ ዘመን የካህናቱና የወንድሞቻቸው መሪዎች ነበሩ።
8ሌዋውያኑም፦ ኢያሱ፥ ቢኒዊ፥ ቃድሚኤል፥ ሼሬብያ፥ ይሁዳና ከወንድሞቹ ጋር በመሆን የምስጋና መዝሙር ኃላፊ የነበረው ማታንያ። 9ወንድሞቻቸው ባቅቡቅያና ዑኖ በአገልግሎቱ ጊዜ በፊት ለፊታቸው ይቆሙ#12፥9 ይቆሙ የሚለው በዕብራይስጡ የለም። ነበር። 10ኢያሱም ዮያቂምን ወለደ፥ ዮያቂም ኤልያሺብን ወለደ፥ ኤልያሺብ ዮያዳዕን ወለደ፥ 11ዮያዳዕ ዮናታንን ወለደ፥ ዮናታን ያዱዓን ወለደ። 12#ነህ. 10፥3-9፤ 12፥1-6።በዮያቂም ዘመን የአባቶች መሪዎች ካህናቱ እነዚህ ነበሩ፦ ከሥራያ ቤተሰብ#12፥12 ቤተሰብ የሚለው በዕብራይስጡ የለም። ምራያ፥ ከኤርምያስ ሐናንያ፥ 13ከዕዝራ ምሹላም፥ ከአማርያ ይሆሐናን፥ 14ከምሉኪ ዮናታን፥ ከሽባንያ ዮሴፍ፥ 15ከሐሪም ዓድና፥ ከምራዮት ሔልቃይ፥ 16ከዒዶ ዘካርያስ፥ ከጊንቶን ምሹላም፥ 17ከአቢያ ዚክሪ፥ ከሚንያሚን፥ ከሞዓድያ፥ ፒልጣይ፥ 18ከቢልጋ ሻሙዓ፥ ከሽማዕያ ይሆናታን፥ 19ከዮያሪብ ማትናይ፥ ከይዳዕያ ዑዚ፥ 20ከሳላይ ቃላይ፥ ከዓሞቅ ዔቤር፥ 21ከሒልቂያ ሐሻብያ፥ ከይዳዕያ ናትናኤል።
22ከሌዋውያኑም በኤልያሺብ፥ ዮያዳዕ፥ ዮሐናን፥ ያዱዓ ዘመን የአባቶች መሪዎችና ካህናቱ በፋርሳዊው በዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ተመዝግበው ነበር። 23የሌዊ ልጆች የአባቶች መሪዎች እስከ ኤልያሺብ ልጅ እስከ ዮሐናን ዘመን ድረስ በታሪክ መጽሐፍ ተመዝግበው ነበር። 24#ዕዝ. 2፥40።የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሻብያ፥ ሼሬብያ፥ የቃድሚኤል ልጅ ኢያሱና ወንድሞቻቸው ደግሞ ከፊት ለፊታቸው ሆነው የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ክፍል በክፍል ትይዩ ሆነው ያወድሱና ያመሰግኑ ነበር። 25#ነህ. 11፥17።ማታንያ፥ ባቅቡቅያ፥ አብድዩ#12፥25 ዕብራይስጡ “ዖባድያ” ይለዋል።፥ ምሹላም፥ ጣልሞን፥ ዓቁብ በበሮቹ አጠገብ የሚገኙትን ዕቃ ቤቶች የሚጠብቁ በር ጠባቂዎች ነበሩ። 26እነዚህ በዮፃዳቅ ልጅ በኢያሱ ልጅ በዮያቂም ዘመንና በገዢው በነህምያና በጸሐፊው በካህኑ በዕዝራ ዘመን ነበሩ።
የከተማው ቅጥር የምረቃ በዓል መደረጉ
27የኢየሩሳሌም ቅጥር ሲመረቅ ምረቃውን በደስታ፥ በምስጋና፥ በመዝሙር፥ በጸናጽል፥ በበገናና በክራር ለማክበር ሌዋውያኑን ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በየሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ፈለጉ። 28የመዘምራኑ ልጆች ከኢየሩሳሌም ዙሪያና ከነጦፋውያን መንደሮች፥ ተሰበሰቡ፤ 29መዘምራኑም በኢየሩሳሌም ዙሪያ መንደሮች ሠርተው ነበርና ከቤትጌልገላም፥ ከጌባና ከዓዝሞት እርሻዎች ተሰበሰቡ። 30ካህናቱና ሌዋውያኑም ራሳቸውን አነጹ፤ ሕዝቡን፥ በሮቹንና ቅጥሩንም አነጹ።
31የይሁዳንም አለቆች ወደ ቅጥሩ ላይ አወጣኋቸው፥ አመስጋኞቹንም በሁለት ታላላቅ ተርታ አቆምኋቸው፥ አንዱም ወደ ቀኝ በቅጥሩ ላይ ወደ ጉድፍ መጣያው በር ሄደ። 32ከእነርሱም በኋላ ሆሻዕያና የይሁዳ መሪዎች እኩሌታ ሄዱ፥ 33አዛርያ፥ ዕዝራ፥ ምሹላም፥ 34ይሁዳ፥ ብንያም፥ ሸማዕያና ኤርምያስ፥ 35መለከት የያዙ ጥቂት የካህናቱ ልጆች፥ የአሳፍ ልጅ፥ የዛኩር ልጅ፥ የሚካያ ልጅ፥ የማታንያ ልጅ፥ የሸማዕያ ልጅ፥ የዮናታን ልጅ ዘካርያስ፥ 36ወንድሞቹም ሸማዕያ፥ ዓዛርኤል፥ ሚላላይ፥ ጊላላይ፥ መዓይ፥ ናትናኤል፥ ይሁዳና ሐናኒ የእግዚአብሔር ሰው የዳዊትን የዜማ መሣሪያ ይዘው ሄዱ፤ ጸሐፊው ዕዝራም በፊታቸው ነበረ። 37“በምንጭ በር” አቅንተው ሄዱ፤ በዳዊትም ከተማ ደረጃ፥ በቅጥሩም መውጫ፥ ከዳዊትም ቤት በላይ እስከ ውኃው በር ድረስ በምሥራቅ በኩል ሄዱ።
38ከፊት ይሄድ የነበረው ሁለተኛው የምስጋና መዘምራን ክፍል ነበር፤ እኔና የሕዝቡ እኩሌታ በስተ ኋላቸው ነበርን፤ በቅጥሩም ላይ፥ ከ “የእቶኑ ግንብ” በላይ እስከ “ሰፊው ቅጥር” ድረስ፥ 39ከ “ኤፍሬም በር” በላይ፥ ከ “አሮጌው በር” በላይ፥ በ “ዓሣ በር” በ “ሐናንኤል ግንብ”፥ በሃሜአ ግንብ እስከ በጎች በር ድረስ ሄዱ፥ በዘበኞችም በር አጠገብ ቆሙ። 40ሁለቱ የምስጋና መዘምራን ክፍሎች በእግዚአብሔር ቤት ቆሙ፥ እኔና ከመሪዎቹ እኩሌታ በተጨማሪ፥ 41ካህናቱ ኤልያቂም፥ መዕሤያ፥ ሚንያሚን፥ ሚካያ፥ ኤልዮዕናዪ፥ ዘካርያስ፥ ሐናንያ መለከት ይዘው፥ 42መዕሤያ፥ ሽማዕያ፥ አልዓዛር፥ ኡዚ፥ ይሆሐናን፥ ማልኪያ፥ ዔላም፥ ዓዜር ቆምን። መዘምራኑም በዪዝራሕያ መሪነት በታላቅ ድምፅ ዘመሩ። 43እግዚአብሔር በታላቅ ደስታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በዚያ ቀን ትልቅ መሥዋዕት አቀረቡ፥ ደስም አላቸው፤ ሴቶቹና ልጆቹም ደግሞ ደስ አላቸው፤ የኢየሩሳሌምም ደስታ ከሩቅ ተሰማ።
የቤተ መቅደስ ኃላፊነቶች
44 # 1ዜ.መ. 23—26፤ 2ዜ.መ. 8፥14። በዚያን ቀን በይሁዳም በአገልጋዮቹ ካህናትና ሌዋውያን ደስ ስላላቸው፥ የካህናቱንና የሌዋውያኑን እድል ፈንታ እንደ ሕጉ ከከተሞች እርሻዎች ያከማቹ ዘንድ ለእጅ ማንሣት ቁርባንና ለበኵራት ለአሥራትም በየዕቃ ቤቶቹ ላይ በዚያ ቀን ሰዎች ተሾሙ። 45እነርሱም መዘምራኑና በረኞቹም የአምላካቸውን ሥርዓት የመንጻታቸውንም ሥርዓት እንደ ዳዊትና እንደ ልጁ እንደ ሰሎሞን ትእዛዝ ጠበቁ። 46#2ዜ.መ. 29፥30፤ 35፥15።አስቀድሞም በዳዊትና በአሳፍ ዘመን እግዚአብሔርን በዜማ ለማመስገንና ለማክበር የመዘምራን አለቆች ነበሩ። 47#ነህ. 10፥39፤ 13፥10-11፤ ዘኍ. 18፥26።እስራኤልም ሁሉ በዘሩባቤልና በነህምያ ዘመን ለመዘምራኑና ለበረኞቹ እድል ፈንታቸውን በየዕለቱ ይሰጡ ነበር፥ የተቀደሰውንም ነገር ለሌዋውያን ሰጡ፥ ሌዋውያኑም ከተቀደሰው ነገር ለአሮን ልጆች ሰጡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ