የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 26:6-30

የማቴዎስ ወንጌል 26:6-30 መቅካእኤ

ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በራሱ ላይም አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቆጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና።” ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህችን ሴት ለምን ታስጨንቁአታላችሁ? ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ይህን ሽቶ በሰውነቴ ላይ በማፍሰስ ለቀብሬ አደረገችው። እውነት እላችኋለሁ ይህ የምሥራች በሚሰበክበት በመላው ዓለም፥ ይህ እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለመታሰቢያዋ ይነገራል።” በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ እንዲህ አላቸው “አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ ምን ትሰጡኛላችሁ?” እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አለ “ወደ ከተማ ወደ አንድ ሰው ሄዳችሁ ‘መምህሩ እንዲህ ይላል፥ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በአንተ ቤት አደርጋለሁ ይላል’ በሉት።” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካውንም አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም ሳሉ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከእኔ ጋር እጁን በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠልቀው፥ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ” አለው። ሲበሉም ሳሉ ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ይህ ነው። በአባቴ መንግሥት አዲሱን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ወይን አልጠጣም እላችኋለሁ።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረዘይት ወጡ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች