የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 26:6-30

ማቴዎስ 26:6-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ አንድ ብልቃጥ የአልባስጥሮስ ሽቱ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን በተመለከቱ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ሽቱው በብዙ ዋጋ ተሸጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ሲቻል!” ኢየሱስ ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች፤ ድኾች ምን ጊዜም ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። ሽቱውን በሰውነቴ ላይ ማፍሰሷ፣ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቧልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን እራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ በማእድ ተቀመጠ፤ በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም እጅግ ዐዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋራ እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው። እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “ዕንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋራ በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከአሁን ጀምሮ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።

ማቴዎስ 26:6-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡና “ይህ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና፤” አሉ። ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው “መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።” በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ “ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ?” እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ?” አሉት። እርሱም “ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል’ በሉት፤” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል፤” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ፤” አለው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤” አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፤ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣም።” መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።

ማቴዎስ 26:6-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቍኦጡና፦ ይህ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና አሉ። ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል። በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፦ ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት። እርሱም፦ ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ፦ መምህር፦ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።

ማቴዎስ 26:6-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እነሆ፥ ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበረ። በዚያም ኢየሱስ በማእድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ሽቶውንም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን አይተው ተቈጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሽቶ ለምን በከንቱ ባከነ? ይህ ሽቶ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድኾች ሊሰጥ ይችል ነበር!” ኢየሱስም ይህን ማለታቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እዚህ አልገኝም። እርስዋ ይህን ሽቶ በእኔ ላይ ማፍሰስዋ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው። በእውነት እላችኋለሁ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያዋ ይነገርላታል።” በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው አስቀሮታዊው ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ሄደና “ኢየሱስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አለ። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ሰጡት እርሱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “የፋሲካ በዓልን ራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “ወደ ከተማው ስትገቡ ወደምታገኙት ሰው ቤት ሂዱና ‘መምህር ጊዜዬ ቀርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በዓል ራት የምበላው በአንተ ቤት ነው ይላል’ በሉት” አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ የፋሲካውንም ራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። ሲበሉም ኢየሱስ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” አለ። ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር በጣም አዝነው፥ እያንዳንዳቸው ጌታ ሆይ፥ “እኔ እሆን?” እያሉ ይጠይቁት ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ከእኔ ጋር በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠቅሰው ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰው ልጅን አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፥ “መምህር ሆይ! እኔ እሆን?” አለ። ኢየሱስም፥ “አንተ እንዳልከው ነው” አለው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ እንዲህ ሲል ሰጣቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጽዋ ጠጡ፤ ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።

ማቴዎስ 26:6-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በራሱ ላይም አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቆጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና።” ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህችን ሴት ለምን ታስጨንቁአታላችሁ? ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ይህን ሽቶ በሰውነቴ ላይ በማፍሰስ ለቀብሬ አደረገችው። እውነት እላችኋለሁ ይህ የምሥራች በሚሰበክበት በመላው ዓለም፥ ይህ እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለመታሰቢያዋ ይነገራል።” በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ እንዲህ አላቸው “አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ ምን ትሰጡኛላችሁ?” እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አለ “ወደ ከተማ ወደ አንድ ሰው ሄዳችሁ ‘መምህሩ እንዲህ ይላል፥ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በአንተ ቤት አደርጋለሁ ይላል’ በሉት።” ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካውንም አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም ሳሉ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከእኔ ጋር እጁን በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠልቀው፥ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ” አለው። ሲበሉም ሳሉ ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አለ። ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ይህ ነው። በአባቴ መንግሥት አዲሱን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ወይን አልጠጣም እላችኋለሁ።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረዘይት ወጡ።