የማቴዎስ ወንጌል 26
26
ኢየሱስን ለመግደል የተደረገ ሤራ
(ማር. 14፥1-2፤ ሉቃ. 22፥1-2፤ ዮሐ. 11፥45-53)
1እንዲህም ሆነ፤ ኢየሱስ እነዚህን ቃሎች ሁሉ ተናግሮ ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 2#ዘፀ. 12፥1-27።“ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል ተላልፎ ይሰጣል።”
3በዚያን ጊዜ ሊቃነ ካህናትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህኑ ግቢ ተሰበሰቡ፤ 4ኢየሱስን በተንኰል ይዘው ሊገድሉት ተማከሩ፤ 5ነገር ግን “በሕዝቡ መካከል ሁከት እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” አሉ።
ኢየሱስን ሽቶ ስለቀባችው ሴት
(ማር. 14፥3-9፤ ዮሐ. 12፥1-8)
6ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ 7#ሉቃ. 7፥37፤38።በማዕድም ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በራሱ ላይም አፈሰሰችው። 8ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቆጡና እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? 9ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና።” 10ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው “ይህችን ሴት ለምን ታስጨንቁአታላችሁ? ለእኔ መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና። 11#ዘዳ. 15፥11።ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ 12እርሷ ይህን ሽቶ በሰውነቴ ላይ በማፍሰስ ለቀብሬ አደረገችው። 13እውነት እላችኋለሁ ይህ የምሥራች በሚሰበክበት በመላው ዓለም፥ ይህ እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለመታሰቢያዋ ይነገራል።”
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት እንደተስማማ
(ማር. 14፥10-11፤ ሉቃ. 22፥3-6)
14በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ 15#ዘካ. 11፥12።እንዲህ አላቸው “አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ ምን ትሰጡኛላችሁ?” እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። 16ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
ኢየሱስ የፋሲካን እራት ከሐዋርያቱ ጋር እንደ በላ
(ማር. 14፥12-21፤ ሉቃ. 22፥7-14፤21-23፤ ዮሐ. 13፥21-30)
17በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። 18እርሱም እንዲህ አለ “ወደ ከተማ ወደ አንድ ሰው ሄዳችሁ ‘መምህሩ እንዲህ ይላል፥ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በአንተ ቤት አደርጋለሁ ይላል’ በሉት።” 19ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ፋሲካውንም አዘጋጁ።
20በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። 21ሲበሉም ሳሉ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። 22እጅግም አዝነው እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ! እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። 23#መዝ. 41፥9።እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከእኔ ጋር እጁን በሳሕኑ ውስጥ የሚያጠልቀው፥ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል። 24የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” 25አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ “መምህር ሆይ! እኔ እሆንን?” አለ፤ “አንተ አልህ” አለው።
የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት
(ማር. 14፥22-26፤ ሉቃ. 22፥15-20፤ 1ቆሮ. 11፥23-25)
26ሲበሉም ሳሉ ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና “እንካችሁ፥ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አለ። 27ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህ ብሎ ሰጣቸው “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ 28#ዘፀ. 24፥8፤ ኤር. 31፥31-34።ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የኪዳን ደሜ ይህ ነው። 29በአባቴ መንግሥት አዲሱን ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ ከዚህ ወይን አልጠጣም እላችኋለሁ።” 30መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረዘይት ወጡ።
ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ተናገረ
(ማር. 14፥27-31፤ ሉቃ. 22፥31-34፤ ዮሐ. 13፥36-38)
31 #
ዘካ. 13፥7። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአልና፥ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ 32#ማቴ. 28፥16።ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” 33ጴጥሮስም “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ሲል መለሰለት። 34ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። 35ጴጥሮስም “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ፥ ከቶ አልክድህም፤” አለው። ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ እንደዚሁ አሉ።
ኢየሱስ በጌቴሴማኒ እንደ ጸለየ
(ማር. 14፥32-42፤ ሉቃ. 22፥39-46)
36በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። 37ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ይዞ ሄደና ማዘንና መጨነቅ ጀመረ። 38“ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ እዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው። 39ወደ ፊት ጥቂት እልፍ ብሎ በፊቱ ተደፋና እንዲህ ሲል ጸለየ “አባቴ! የሚቻል ከሆነ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ አይሁን።” 40ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን? 41ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፥ ጸልዩም፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” 42እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ “አባቴ ሆይ! ይህንን ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ፥ ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ጸለየ። 43ዳግመኛ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና። 44እንደገና ትቶአቸው ሄደ፤ ያንኑ ቃል ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጸለየ። 45ከዚህ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው “ከእንግዲህስ ተኙ፥ ዕረፉም፤ እነሆ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። 46ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።”
የኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ
(ማር. 14፥43-50፤ ሉቃ. 22፥47-53፤ ዮሐ. 18፥3-12)
47ይህንም ገና ሲናገር ሳለ፥ እነሆ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ዱላ ይዘው ከእርሱ ጋር መጡ። 48አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 49ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። 50ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! ለምን መጣህ?” አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡና እጃቸውን በኢየሱስ ላይ ጫኑ፥ ያዙትም። 51እነሆ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህኑን ባርያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው። 52በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና። 53ወይስ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት አሁን ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? 54እንዲህ ከሆነ ‘እንደዚህ መሆን አለበት’ የሚሉት መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማል?” 55#ሉቃ. 19፥47፤ 21፥37።በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ወጣችሁን? ዕለት በዕለት በመቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር ሳለሁ አልያዛችሁኝም። 56ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው የነቢያት መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።
ኢየሱስ በአይሁድ የፍርድ ሸንጎ ፊት እንደ ቆመ
(ማር. 14፥53-65፤ ሉቃ. 22፥54-55፤63-71፤ ዮሐ. 18፥13-14፤19-24)
57ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። 58ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህኑ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ለማየት ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። 59ሊቃነ ካህናትና ሸንጎው ሁሉ ሊገድሉት ፈልገው በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ 60ነገር ግን አላገኙም፤ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢመጡም ምንም አላገኙም፤ በመጨረሻም ሁለት መጥተው፥ 61#ዮሐ. 2፥19።“ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል፤” አሉ። 62ሊቀ ካህኑም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። 63ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህኑም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከሆንህ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” አለው። 64#ዳን. 7፥13።ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥና በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። 65#ዘሌ. 24፥16።በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህኑ ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ “ተሳድቦአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን መያዝ ለምን ያስፈልገናል? እነሆ አሁን ስድቡን ሰምታችኋል፤ 66ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። 67#ኢሳ. 50፥6።በዚያን ጊዜ ፊቱ ላይ ተፉበት፥ መቱት፥ በጥፊም መቱት 68እንዲህም አሉት “ክርስቶስ ሆይ! እስቲ ትንቢት ተናገርልን፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?”
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ ካደ
(ማር. 14፥66-72፤ ሉቃ. 22፥56-62፤ ዮሐ. 18፥15-18፤25-27)
69ጴጥሮስም ከቤት ውጪ በግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው። 70እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቀውም” ብሎ በሁሉም ፊት ካደ። 71ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ ሌላዪቱ አየችውና በዚያ ለነበሩት “ይህም ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ” አለቻቸው። 72“ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ እየማለ ካደ። 73ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያ ቆመው የነበሩት ጠጋ ብለው ጴጥሮስን “በእውነት አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤ አነጋገርህ ያስታውቅብሃልና” አሉት። 74በዚያን ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ ይራገምና ይምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። 75ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ የተናገረውን የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 26: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ