የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 25

25
የዐሥሩ ደናግል ምሳሌ
1 # ሉቃ. 12፥35። “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ደናግል ትመስላለች። 2ከእነርሱም አምስቱ ሞኞች አምስቱ ደግሞ ብልሆች ነበሩ። 3ሞኞቹ መብራታቸውን ይዘው ነገር ግን ዘይት አልያዙም ነበር፤ 4ብልሆቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮ ዘይት ይዘው ነበር። 5ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ፥ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። 6እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ ‘እነሆ ሙሽራው፤ ልትቀበሉት ውጡ’ የሚል ጩኸት ተሰማ። 7በዚያን ጊዜ እነዚያ ደናግል ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። 8ሞኞቹ ብልሆቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ነውና ከዘይታችሁ ስጡን’ አሉአቸው። 9ብልሆቹ ግን ‘ለእኛና ለእናንተ ላይበቃ ይችላል፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። 10ሊገዙ በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ከእርሱ ጋር ወደ ሰርጉ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። 11#ሉቃ. 13፥25።ከዚህ በኋላ የቀሩቱ ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ አሉት። 12እርሱ ግን ‘እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም’ ሲል መለሰላቸው። 13ቀኑንና ሰዓቱን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ።
የመክሊቶቹ ምሳሌ
(ሉቃ. 19፥11-27)
14 # ሉቃ. 19፥11-27። “እንግዲህ ወደ ሌላ አገር ሊሄድ ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት እንደሰጣቸው ሰው ይሆናልና፤ 15ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፥ ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለአንዱ ሁለት፥ ለአንዱ ደግሞ አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 16አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት አተረፈ፤ 17እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። 18አንድ የተቀበለው ግን ሄደና ምድርን ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። 19ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባርያዎች ጌታ መጥቶ ከእነርሱ ጋር መተሳሰብ ጀመረ። 20አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አምጥቶ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። 21ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። 22ባለ ሁለት መክሊቱም ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። 23ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። 24አንድ መክሊት የተቀበለውም ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንህ አውቃለሁ፤ 25ስለፈራሁም ሄጄ መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ የራስህ ይኸውልህ’ አለ። 26ጌታውም እንዲህ ሲል መለሰለት ‘አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባርያ፥ ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንሁበትም እንደምሰበስብ ታውቃለህን? 27ስለዚህ ገንዘቤን ለገንዘብ ለዋጮች መስጠት ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ያለኝን ከነወለዱ እወስደው ነበር። 28በሉ እንግዲህ መክሊቱን ውሰዱበትና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፤ 29#ማቴ. 13፥12፤ ማር. 4፥25፤ ሉቃ. 8፥18።ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 30#ማቴ. 8፥12፤ 22፥13፤ ሉቃ. 13፥28።የማይረባውን ባርያ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’
ስለ አሕዛብ ፍርድ
31 # ማቴ. 16፥27፤ ማቴ. 19፥28። “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ 32አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፤ 33በጎቹን በቀኙ ፍየሎቹን ደግሞ በግራው ያቆማቸዋል። 34ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል ‘እናንተ የአባቴ ቡሩካን! ኑ! ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። 35#ሲራ. 7፥32-36።ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ 36ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ታምሜ ጠይቃችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’ 37ጻድቃኑም እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል ‘ጌታ ሆይ! መቼ ተርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ? 38መቼ እንግዳ ሆነህ አየንህና ተቀበልንህ? መቼ ታርዘህ አየንህና አለበስንህ? 39መቼ ታመህ ወይም ታስረህ አየንህና ወደ አንተ መጥተን ጠየቅንህ?’ 40ንጉሡም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው።’ 41ከዚህ በኋላ በግራው ያሉትን ደግሞ እንዲህ ይላቸዋል ‘እናንተ የተረገማችሁ! ከእኔ ወዲያ ራቁ! ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ። 42ተርቤ አላበላችሁኝምና፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፤ 43እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’ 44እነርሱም እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል ‘ጌታ ሆይ! ተርበህ ወይም ተጠምተህ ወይም እንግዳ ሆነህ ወይም ታርዘህ ወይም ታመህ ወይም ታስረህ መቼ አየንህና አላገለገልንህም?’ 45ያንጊዜ እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል ‘እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ያላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ እንዳላደረጋችሁት ነው።’ 46#ዳን. 12፥2።እነዚህ ወደ ዘለዓለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማቴዎስ ወንጌል 25