ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ አንድ ብልቃጥ የአልባስጥሮስ ሽቱ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱ ይህን በተመለከቱ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድን ነው? ሽቱው በብዙ ዋጋ ተሸጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ሲቻል!” ኢየሱስ ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች፤ ድኾች ምን ጊዜም ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። ሽቱውን በሰውነቴ ላይ ማፍሰሷ፣ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቧልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን እራት አዘጋጁ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ በማእድ ተቀመጠ፤ በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም እጅግ ዐዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋራ እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤ የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው። እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “ዕንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋራ በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከአሁን ጀምሮ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።
ማቴዎስ 26 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 26
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 26:6-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos