የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 20:20-34

የማቴዎስ ወንጌል 20:20-34 መቅካእኤ

በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ከልጆችዋ ጋር ወደ እርሱ ቀረበች። እርሱም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም “እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ እዘዝ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” እነርሱም “እንችላለን” አሉት። እርሱም “ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ መስጠት የእኔ አይደለም ነገር ግን እርሱ በአባቴ ለተዘጋጀላቸው ነው፤” አላቸው። ዐሥሩም ይህንን በሰሙ ጊዜ በሁለቱም ወንድማማቾች ተቆጡ። ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው “የአሕዛብ አለቆች ጌትነታቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታላላቆቹም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታውቃላችሁ። በእናንተ መካከል እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተም መካከል ፊተኛ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባርያ ይሁን፤ የሰው ልጅም ሊያገለግል፥ ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ከኢያሪኮ ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆ፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንደሚያልፍ በሰሙ ጊዜ “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው” አሉት። ኢየሱስም አዘነላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ አዩ፥ ተከተሉትም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች