የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 20:20-34

የማቴዎስ ወንጌል 20:20-34 አማ05

ከዚህ በኋላ የዘብዴዎስ ልጆች እናት፥ ከልጆችዋ ጋር ወደ ኢየሱስ ቀረበችና በፊቱም ተንበርክካ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። ኢየሱስም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርስዋም “በመንግሥትህ እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ፥ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ!” አለችው። ኢየሱስ ግን “እናንተ የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ በቅርብ ጊዜ የምጠጣውን የመከራ ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎ እንችላለን!” አሉ። ኢየሱስም “በእርግጥ እኔ የምጠጣውን የመከራ ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን ሰዎችን በቀኜና በግራዬ እንዲቀመጡ የማደርገው እኔ አይደለሁም፤ ይህ ቦታ የሚሰጠው አባቴ ላዘጋጀላቸው ሰዎች ነው።” የቀሩት ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት ይህን ልመና በሰሙ ጊዜ በሁለቱ ወንድማማች ላይ ተቈጡ። ኢየሱስ ግን ሁሉንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው። “የአሕዛብ አለቆች የሕዝቦቻቸው ገዢዎች ናቸው፤ መሪዎቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ታውቃላችሁ። በእናንተስ መካከል እንዲህ መሆን አይገባም። ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን። እንዲሁም ከእናንተ የበላይ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባሪያ ይሁን። የሰው ልጅም ለማገልገልና ብዙዎችን ለማዳን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ከዚህ በኋላ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተከተሉት። እነሆ፥ በመንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዕውሮች በዚያ በኩል የሚያልፈው ኢየሱስ መሆኑን በሰሙ ጊዜ፥ “ጌታ የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ሕዝቡም “ዝም በሉ!” ብለው ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ አድርግልን!” አሉት። ኢየሱስም ራራላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ ዐይኖቻቸው አዩ፤ እነርሱም ኢየሱስን ተከተሉት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች