ከዚያም፣ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋራ ወደ ኢየሱስ ቀርባ በፊቱ ተንበርክካ እየሰገደች፣ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። እርሱም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም፣ “እነዚህ ሁለት ልጆቼ፣ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ ፍቀድ” አለችው። ኢየሱስም መልሶ፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፣ “እንችላለን” አሉት። እርሱም፣ “ከጽዋዬ በርግጥ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን በቀኜና በግራዬ መቀመጥ አባቴ ላዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምፈቅደው ነገር አይደለም” አላቸው። ዐሥሩም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ሁለቱን ወንድማማቾች ተቈጧቸው። ኢየሱስ ግን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ገዦች በሕዝባቸው ላይ ጌቶች እንደሚሆኑ፣ ባለሥልጣኖቻቸውም በእነርሱ ላይ እንደሚሠለጥኑባቸው ታውቃላችሁ፤ በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም። ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን፤ ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቷልና።” ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። በዚያም ሁለት ዐይነ ስውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው ነበር፤ ኢየሱስም በዚያ ማለፉን ሲሰሙ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” በማለት ጮኹ። ሕዝቡም በግሣጼ ቃል ዝም እንዲሉ ነገሯቸው፤ እነርሱ ግን አምርረው በመጮኽ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” አሉ። ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ” አሉት። ኢየሱስም ራራላቸው፤ ዐይኖቻቸውንም ዳሰሰ፣ ወዲያው አዩ፤ ተከተሉትም።
ማቴዎስ 20 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 20
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 20:20-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos