ማቴዎስ 20:20-34
ማቴዎስ 20:20-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም፣ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋራ ወደ ኢየሱስ ቀርባ በፊቱ ተንበርክካ እየሰገደች፣ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። እርሱም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም፣ “እነዚህ ሁለት ልጆቼ፣ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ ፍቀድ” አለችው። ኢየሱስም መልሶ፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፣ “እንችላለን” አሉት። እርሱም፣ “ከጽዋዬ በርግጥ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን በቀኜና በግራዬ መቀመጥ አባቴ ላዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምፈቅደው ነገር አይደለም” አላቸው። ዐሥሩም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ሁለቱን ወንድማማቾች ተቈጧቸው። ኢየሱስ ግን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ገዦች በሕዝባቸው ላይ ጌቶች እንደሚሆኑ፣ ባለሥልጣኖቻቸውም በእነርሱ ላይ እንደሚሠለጥኑባቸው ታውቃላችሁ፤ በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም። ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን፤ ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቷልና።” ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። በዚያም ሁለት ዐይነ ስውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው ነበር፤ ኢየሱስም በዚያ ማለፉን ሲሰሙ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” በማለት ጮኹ። ሕዝቡም በግሣጼ ቃል ዝም እንዲሉ ነገሯቸው፤ እነርሱ ግን አምርረው በመጮኽ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” አሉ። ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ” አሉት። ኢየሱስም ራራላቸው፤ ዐይኖቻቸውንም ዳሰሰ፣ ወዲያው አዩ፤ ተከተሉትም።
ማቴዎስ 20:20-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ የዘብዴዎስ ልጆች እናት፥ ከልጆችዋ ጋር ወደ ኢየሱስ ቀረበችና በፊቱም ተንበርክካ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። ኢየሱስም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርስዋም “በመንግሥትህ እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ፥ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ!” አለችው። ኢየሱስ ግን “እናንተ የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ በቅርብ ጊዜ የምጠጣውን የመከራ ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎ እንችላለን!” አሉ። ኢየሱስም “በእርግጥ እኔ የምጠጣውን የመከራ ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን ሰዎችን በቀኜና በግራዬ እንዲቀመጡ የማደርገው እኔ አይደለሁም፤ ይህ ቦታ የሚሰጠው አባቴ ላዘጋጀላቸው ሰዎች ነው።” የቀሩት ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት ይህን ልመና በሰሙ ጊዜ በሁለቱ ወንድማማች ላይ ተቈጡ። ኢየሱስ ግን ሁሉንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው። “የአሕዛብ አለቆች የሕዝቦቻቸው ገዢዎች ናቸው፤ መሪዎቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ታውቃላችሁ። በእናንተስ መካከል እንዲህ መሆን አይገባም። ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን። እንዲሁም ከእናንተ የበላይ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባሪያ ይሁን። የሰው ልጅም ለማገልገልና ብዙዎችን ለማዳን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ከዚህ በኋላ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተከተሉት። እነሆ፥ በመንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዕውሮች በዚያ በኩል የሚያልፈው ኢየሱስ መሆኑን በሰሙ ጊዜ፥ “ጌታ የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ሕዝቡም “ዝም በሉ!” ብለው ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ አድርግልን!” አሉት። ኢየሱስም ራራላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ ዐይኖቻቸው አዩ፤ እነርሱም ኢየሱስን ተከተሉት።
ማቴዎስ 20:20-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆችዋ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ እርሱ ቀረበች። እርሱም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርስዋም “እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ፤” አለችው። ኢየሱስ ግን መልሶ “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አለ። “እንችላለን” አሉት። እርሱም “ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም፤” አላቸው። ዐሥሩም ሰምተው በሁለቱ ወንድማማች ተቍኦጡ። ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው “የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ “ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ፥ ማረን” ብለው ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ፥ ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ?” አለ። “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ” አሉት። ኢየሱስም አዘነላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውም አዩና ተከተሉት።
ማቴዎስ 20:20-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆችዋ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ እርሱ ቀረበች። እርሱም፦ ምን ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም፦ እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ አለችው። ኢየሱስ ግን መልሶ፦ የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አለ። እንችላለን አሉት። እርሱም፦ ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም አላቸው። አሥሩም ሰምተው በሁለቱ ወንድማማች ተቍኦጡ። ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን ብለው ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና፦ ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አለ። ጌታ ሆይ፥ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት። ኢየሱስም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፥ ወዲያውም አዩና ተከተሉት።
ማቴዎስ 20:20-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ከልጆችዋ ጋር ወደ እርሱ ቀረበች። እርሱም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም “እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ እዘዝ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” እነርሱም “እንችላለን” አሉት። እርሱም “ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ መስጠት የእኔ አይደለም ነገር ግን እርሱ በአባቴ ለተዘጋጀላቸው ነው፤” አላቸው። ዐሥሩም ይህንን በሰሙ ጊዜ በሁለቱም ወንድማማቾች ተቆጡ። ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው “የአሕዛብ አለቆች ጌትነታቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታላላቆቹም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታውቃላችሁ። በእናንተ መካከል እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተም መካከል ፊተኛ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባርያ ይሁን፤ የሰው ልጅም ሊያገለግል፥ ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ከኢያሪኮ ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆ፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንደሚያልፍ በሰሙ ጊዜ “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ ጮኹ። ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው” አሉት። ኢየሱስም አዘነላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ አዩ፥ ተከተሉትም።