የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 12:1-14

የማቴዎስ ወንጌል 12:1-14 መቅካእኤ

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀመዛሙርቱ ተራቡና እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህንን አይተው “እይ! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ያደርጋሉ፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ካህናት ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት በላ። በሰንበታት በቤተ መቅደስ ያሉ ካህናት ሰንበትን እንደሚያረክሱ ንጹሐንም እንደ ሆኑ በሕጉ አላነበባችሁምን? እላችኋለሁ፥ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ ንጹሐኑን ባልኮነናችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ አልፎ ወደ ምኵራባቸው ገባ። እነሆ አንድ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ሊከሱትም ፈልገው “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው በሰንበት ወደ ጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ማነው? ታዲያ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል።” ከዚያ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም ዘረጋት፤ ያንጊዜ እንደ ሁለተኛዋ ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ተማከሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች