ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ ዐለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን እያደረጉ ነው” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና ዐብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ፣ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፤ ለካህናት እንጂ ለርሱም ሆነ ዐብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ በላ። ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሓን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከስሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዷል?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት፣ በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጐትቶ አያወጣውምን? ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዷል” አላቸው። ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላውም እጁ ደኅና ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ።
ማቴዎስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 12
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 12:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos