ማቴዎስ 12:1-14
ማቴዎስ 12:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው “እነሆ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኀጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ‘ምሕረትን እወዳለሁ፤ መሥዋዕትንም አይደለም፤’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኀጢአት የሌለባቸውን ባልኵኦነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። እነሆም እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል፤” አላቸው። ከዚያም በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። ዘረጋትም፤ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።
ማቴዎስ 12:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ ዐለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን እያደረጉ ነው” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና ዐብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ፣ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፤ ለካህናት እንጂ ለርሱም ሆነ ዐብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ በላ። ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሓን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከስሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዷል?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት፣ በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጐትቶ አያወጣውምን? ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዷል” አላቸው። ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላውም እጁ ደኅና ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ።
ማቴዎስ 12:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው፦ እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኵኦነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና። ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ፦ በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው። ከዚያም በኋላ ሰውየውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።
ማቴዎስ 12:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በስንዴ እርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ርቦአቸው ስለ ነበረ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህን አይተው ኢየሱስን “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ!” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር እርሱም ሆነ አብረውት የነበሩት ሰዎች ሊበሉት ያልተፈቀደውን፥ የተቀደሰ ኅብስት በላ። ደግሞስ ካህናት በሰንበት ቀን በቤተ መቅደስ ሰንበትን ሲጥሱ በደል ሆኖ እንደማይቈጠርባቸው በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? ነገር ግን ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እነሆ፥ እዚህ አለ እላችኋለሁ። ደግሞም ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ምን እንደ ሆነ ብታስተውሉ ኖሮ በደል በሌለባቸው ሰዎች ላይ ባልፈረዳችሁም ነበር። እንዲያውም የሰው ልጅ የሰንበትም ጌታ ነው።” ኢየሱስ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ወደ ምኲራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስን የሚከሱበትን ምክንያት የፈለጉ አንዳንድ ሰዎች “በሰንበት ቀን በሽተኛን መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው፥ በጉ በሰንበት ቀን በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ስቦ የማያወጣው ማነው? ታዲያ፥ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረግ የተፈቀደ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እጀ ሽባውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋው ጊዜ እጁ ድኖ ልክ እንደ ደኅነኛው እጅ ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጥተው ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተማከሩ።
ማቴዎስ 12:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀመዛሙርቱ ተራቡና እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህንን አይተው “እይ! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ያደርጋሉ፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ ዳዊት ያደረገውን አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ካህናት ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት በላ። በሰንበታት በቤተ መቅደስ ያሉ ካህናት ሰንበትን እንደሚያረክሱ ንጹሐንም እንደ ሆኑ በሕጉ አላነበባችሁምን? እላችኋለሁ፥ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ ንጹሐኑን ባልኮነናችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” ከዚያ አልፎ ወደ ምኵራባቸው ገባ። እነሆ አንድ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ሊከሱትም ፈልገው “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው በሰንበት ወደ ጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ማነው? ታዲያ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል።” ከዚያ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም ዘረጋት፤ ያንጊዜ እንደ ሁለተኛዋ ደህና ሆነች። ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ተማከሩ።