የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 12:1-14

የማቴዎስ ወንጌል 12:1-14 አማ05

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በስንዴ እርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ርቦአቸው ስለ ነበረ የስንዴ እሸት እየቀጠፉ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያን ይህን አይተው ኢየሱስን “ተመልከት! ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ!” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር እርሱም ሆነ አብረውት የነበሩት ሰዎች ሊበሉት ያልተፈቀደውን፥ የተቀደሰ ኅብስት በላ። ደግሞስ ካህናት በሰንበት ቀን በቤተ መቅደስ ሰንበትን ሲጥሱ በደል ሆኖ እንደማይቈጠርባቸው በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? ነገር ግን ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እነሆ፥ እዚህ አለ እላችኋለሁ። ደግሞም ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ምን እንደ ሆነ ብታስተውሉ ኖሮ በደል በሌለባቸው ሰዎች ላይ ባልፈረዳችሁም ነበር። እንዲያውም የሰው ልጅ የሰንበትም ጌታ ነው።” ኢየሱስ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ወደ ምኲራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጀ ሽባ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስን የሚከሱበትን ምክንያት የፈለጉ አንዳንድ ሰዎች “በሰንበት ቀን በሽተኛን መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው፥ በጉ በሰንበት ቀን በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ስቦ የማያወጣው ማነው? ታዲያ፥ ከበግ ይልቅ ሰው እንዴት አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረግ የተፈቀደ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እጀ ሽባውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እርሱም በዘረጋው ጊዜ እጁ ድኖ ልክ እንደ ደኅነኛው እጅ ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጥተው ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚገድሉት ተማከሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች