የሉቃስ ወንጌል 9:28-56

የሉቃስ ወንጌል 9:28-56 መቅካእኤ

ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ፥ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ ፀዳል አብረቅርቆ ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ፤ በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ሊፈጽመው ስላለ ሞቱ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ነበር፤ ነቅተውም ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከእርሱም ሁለቱ ሰዎች በተለዩ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ “አቤቱ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ፥ አንድም ለሙሴ፥ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤” አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ሳለ ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም፦ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። እነርሱም ዝም አሉ፥ ያዩትንም ምንም ዓይነት ነገር በነዚያ ቀናት ለማንም አላወሩም። በማግስቱም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኘው። እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ፦ “መምህር ሆይ! ለእኔ ብቸኛ ልጄ ነውና፥ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። እነሆም፥ ርኩስ መንፈስ ይይዘዋል፤ ድንገትም ይጮኻል፤ አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ አድቅቆ በጭንቅ ይለቀዋል፤ ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፦ “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው፤” አለ። ልጁም በመምጣት ላይ ሳለ ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው፤ ልጁንም ለአባቱ መልሶ ሰጠው። ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ ሳሉ፥ እርሱ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “የሰው ልጅ በሰው እጅ ተላልፎ የሚሰጥ ስለሆነ እናንተ እነዚህን ቃላት በጆሮዎቻችሁ አኑሩ፤” አለ። እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፤ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህም ነገር እርሱን ለመጠየቅ ፈሩ። ከእነርሱም መካከል ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ አንድ ሕፃን ወሰደና፥ በአጠገቡም አቁሞት፦ “ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ በእናንተ መካከል ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና፤” አላቸው። ዮሐንስም መልሶ፦ “አቤቱ! አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው” አለው። ኢየሱስ ግን፦ “የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት፤” አለው። ኢየሱስ የሚያርግበት ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፤ እርሱም አስቀድሞ መልክተኞችን ላከ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንዲት የሳምራውያን መንደር ገቡ፤ ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ ፊቱን አቅንቶ ስለ ነበረ የመንደሩ ሰዎች አልተቀበሉትም። ደቀመዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲበላቸው እንድናዝዝ ትወዳለህን?” አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸው። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።