ኦሪት ዘሌዋውያን 8:14-24

ኦሪት ዘሌዋውያን 8:14-24 መቅካእኤ

የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ እንዲያስተሰርይለትም ቀደሰው። በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ከስባቸው ጋር ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቆዳውንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሙሴ አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ።