ኦሪት ዘሌዋውያን 8

8
የካህን የሹመት ሥርዓት
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅባቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሚቀርበውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ እርሾ ያልነካው ቂጣ የሚቀመጥበትንም መሶብ ውሰድ፤ 3ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።” 4#ዘኍ. 27፥19።ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰበ። 5ሙሴም ማኅበሩን፦ “ጌታ እንዲደረግ ያዘዘው ነገር ይህ ነው” አላቸው።
6ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው። 7#ሲራ. 45፥8-13፤ ዕብ. 5፥1-4፤ 7፥1-28።ልብስም አለበሰው፥ በመርገፍም#8፥7 በሻኩራም በተጌጠ ዝናር አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ የኤፉድ ማንጠልጠያ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ ኤፉዱን አሰረው። 8የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን#8፥8 ኡሪምንና ቱሚምን በመጠቀም ካህናት የጌታን ፈቃድ የሚያውቁበት ቁሳዊ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ በዘኁ 27፥21 1ሳሙ 14፥41፤ 28፥6 ተመልከት. አኖረበት። 9ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል፥ የወርቅ ጉንጉን ሆኖ በቅጠል መልክ የተሠራውን የተቀደሰ አክሊል፥ አደረገ።
10 # ዘፀ. 30፥26። ሙሴም የቅባቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። 11ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ እንዲቀደሱም መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና መቀመጫውን ቀባ። 12#ሲራ. 45፥15።ከቅባቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ እንዲቀደስም ቀባው። 13ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመርገፍም በተጌጠ መታጠቂያ አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው።
14የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 15#ዕብ. 9፥22።አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ እንዲያስተሰርይለትም ቀደሰው። 16#ዘሌ. 3፥4-5፤ 4፥8-11።በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ከስባቸው ጋር ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 17#ዘሌ. 6፥23።ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቆዳውንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ።
18 # ዘሌ. 1፥10-13። ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 19አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። 20አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። 21የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሙሴ አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።
22 # ዘሌ. 7፥37። ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 23#ዘሌ. 14፥14፤ 17።አረደውም፤ ሙሴም ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። 24የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። 25ከዚያም በኋላ ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ 26በጌታ ፊት ካለው እርሾ ያልነካው ቂጣ ከሚቀመጥበት መሶብ አንድ እርሾ ያልገባበት የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም ከዘይት ጋራ የተሰናዳ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። 27#ዘሌ. 7፥30።ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በጌታም ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዛቸው። 28ከዚያም በኋላ ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ የቅድስና መሥዋዕት አድርጎ ሙሴ ከእጃቸው ተቀብሎ በሚቃጥለው መሥዋዕት ላይ በመሠዊያው አቃጠለው። 29ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘው፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከሚቀርበው አውራ በግ የሆነ የሙሴ ድርሻ ነበር።
30 # ዘፀ. 40፥15። ሙሴም ከቅባቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም፥ የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ።
31ሙሴም አሮንንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ ከዚህም ጋር ‘አሮንና ልጆቹ ይበሉታል’ ብዬ እንዳዘዝሁ የቅድስናው መሥዋዕት እንጀራ ከሚቀመጥበት መሶብ ውስጥ ያለውን እንጀራ በዚያ ትበሉታላችሁ። 32ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ። 33እናንተን በቅድስና ማዕረግ ለመሾም ሰባት ቀን ይወስዳልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። 34ዛሬ እንደተደረገው እንዲሁ ለእናንተ ማስተስረያም እንዲደረግ ጌታ አዝዞአል። 35#ዘሌ. 10፥7።እንዳትሞቱም የጌታን ትእዛዝ እየጠበቃችሁ፥ ለሰባት ቀን ሌሊትና ቀን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ትቀመጣላችሁ፤ እኔ እንዲህ ታዝዣለሁና።” 36አሮንና ልጆቹም ጌታ በሙሴ አንደበት ያዘዘውን ቃላት ሁሉ አደረጉ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ