ኦሪት ዘሌዋውያን 23
23
የጌታ በዓላት
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2#ዘኍ. 28—29፤ ዘዳ. 16፥1-17።“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የጌታ በዓላት፥ እነዚህ ናቸው።
ሰንበት፥ ፋሲካ፥ የቂጣ በዓል
3 #
ዘሌ. 19፥3፤ 26፥2፤ ዘፀ. 20፥8-11፤ 23፥12፤ 31፥14-15፤ 34፥21፤ ዘኍ. 28፥9-10፤ ዘዳ. 5፥12-15፤ ሉቃ. 13፥14። “ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይደረግበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለጌታ ሰንበት ነው።
4 #
ዘፀ. 23፥14-19። “እነዚህ የጌታ በዓላት፥ ለእነርሱ በተወሰነላቸው ጊዜ የምታውጁአቸው፥ የተቀደሱ ጉባኤዎች ናቸው። 5#ዘፀ. 12፥1-51፤ ዘኍ. 9፥1-8፤ 28፥16-25፤ ዘዳ. 16፥1-8።በመጀመሪያው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የጌታ ፋሲካ ነው። 6#ዘፀ. 12፥18፤ 13፥3-10፤ 23፥15፤ 34፥18።በዚህም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን ለጌታ የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን እርሾ ያልነካው የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። 7በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 8ሰባት ቀንም ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።”
የበኵራት ፍሬ ቁርባን
9ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከሩን ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤ 11#ዘሌ. 7፥30፤ ዘዳ. 26፥2።እርሱም ነዶውን በጌታ ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው፤ ካህኑ የሚወዘውዘው በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ነው። 12ነዶውንም በወዘወዛችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ለጌታ አቅርቡ። 13የእህልም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ይሁን፤ ለመጠጥም ቁርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የሆነ የወይን ጠጅ ይቅረብ። 14የአምላካችሁን ቁርባን እስከምታመጡበት እስከዚህ ቀን ድረስ እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።
ሰንበት
15 #
ዘፀ. 23፥16፤ 34፥22፤ ዘኍ. 28፥26-31፤ ዘዳ. 16፥9-12። “ለመወዝወዝ ቁርባን ነዶውን ካመጣችሁበት ቀን ከሰንበት በኋላ በማግስቱ ያሉትን ቀኖች ቁጠሩ። እነርሱም ሰባት ሙሉ ሳምንታት ይሁኑ። 16#የሐዋ. 2፥1።እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ ኀምሳ ቀን ቁጠሩ። ከዚያም አዲሱን የእህል ቁርባን ለጌታ አቅርቡ። 17ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ። ለጌታ ለበኵራት ቁርባን እንዲሆን በእርሾ ተቦክቶ ይጋገራል። 18ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ተባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ። ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ሆኖ ከእህል ቁርባናቸውና ከመጠጥ ቁርባናቸው ጋር ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ። 19እንዲሁም አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለአንድነት መሥዋዕት አቅርቡ። 20ካህኑም ከበኩራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ይወዘውዛቸዋል። ለካህኑ ለጌታ የተቀደሱ ይሆናሉ። 21በዚያም ቀን ታውጃላችሁ፤ የተቀደሰ ጉባኤም ታደርጋላችሁ። የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።
22 #
ዘሌ. 19፥9-10። “የምድራችሁንም መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ እስከ እርሻችሁ ድንበር ድረስ ፈጽማችሁ አትሰብስቡ። የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሀውና ለእንግዳው ተዉት። እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”
የመለከት ድምፅ መታሰብያ
23ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 24#ዘኍ. 29፥1-6።“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን ፈጽሞ የምታርፉበት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የምታውጁበት፥ የተቀደሰ ጉባኤ የምታደርጉበት ይሁንላችሁ። 25የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ።”
የማስተስረያ ቀን
26 #
ዘሌ. 16፥29-34። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 27#ዘሌ. 16፥1-34፤ 25፥9፤ ዘኍ. 29፥7-11።“በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ራሳችሁን አዋርዱ፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ። 28በአምላካችሁም በጌታ ፊት ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። 29በዚያም ቀን ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 30በዚያም ቀን ማናቸውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። 31ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። 32ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ ራሳችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን ከማታ ጀምሮ፥ ከማታ እስከ ማታ ድረስ ሰንበታችሁን አድርጉ።”
የዳስ በዓል
33ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 34#ዘፀ. 23፥16፤ 34፥22፤ ዘዳ. 16፥13-15፤ 31፥10፤ 2መቃ. 1፥9፤ ዮሐ. 7፥2።“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለጌታ የዳስ በዓል ነው። 35በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 36ሰባት ቀን ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
37“የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቁርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቁርባን፥ ለጌታም በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን፥ እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው ቀናቸው እንድታቀርቡባቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የጌታ በዓላት እነዚህ ናቸው። 38እነዚህም ከጌታ ሰንበታት ሌላ፥ ለጌታም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለታችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው።
39“በሰባተኛውም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን የምድሪቱን ምርት በሰበሰባችሁ ጊዜ የጌታን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን። 40በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የዘንባባ ዝንጣፊ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በጌታ ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። 41ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለጌታ አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ። 42ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ በእስራኤል ያሉት የአገሩ ተወላጆች ሁሉ በዳሶች ውስጥ ይቀመጣሉ፤ 43በዚህም ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳሶች ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ እንዲያውቁ ነው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” 44ሙሴም የጌታን በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 23: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ