ኦሪት ዘሌዋውያን 14:1-18

ኦሪት ዘሌዋውያን 14:1-18 መቅካእኤ

ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “በመንጻቱ ቀን የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል። ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ለምጽ ካለበት ሰው ላይ ቢጠፋ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው በሕይወት ያሉ ሁለት ንጹሐን ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም እንዲመጣለት ያዝዛል። ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ እንዲታረድ ያዝዛል። በሕይወት ያለውን ወፍ፥ የዝግባውንም እንጨት፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሂሶጱንም ወስዶ ይነክራቸዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው የወፍ ደም ውስጥ ይዘፍቀዋል። ከለምጽ ደዌ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ከዚያም ንጹሕ ነህ ይለዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በተንጣለለው ሜዳ ላይ እንዲበር ይለቀዋል። የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጉሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። በሰባተኛውም ቀን ጠጉሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጉር ሁሉ ይላጫል፤ ከዚያም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል። “በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ለእህሉም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ዘይትም ያለበትን አንድ የሎግ መስፈሪያ ይወስዳል። የሚያነጻውም ካህን የሚነጻውን ሰውና እነዚህን ነገሮች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በጌታ ፊት ያኖራቸዋል። ካህኑም አንዱን ተባት ጠቦት ይወስዳል፤ እርሱንም ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ጎን ለጎንም ዘይቱ ያለበትን የሎግ መስፈሪያውን፤ እነርሱንም ስለ መወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል። የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርድበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ እንደ ኃጢአት መሥዋዕቱም እንዲሁ የበደል መሥዋዕቱ ለካህኑ ይሆናል፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ይወስዳል፤ እርሱም የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። ካህኑም ከሎግ መስፈሪያው ውስጥ ያለውን ዘይት ወስዶ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈስሰዋል። ካህኑም በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያለውን ዘይት በቀኝ ጣቱ ነክሮ ከዘይቱ በጌታ ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ ከተረፈው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት፥ የበደልም መሥዋዕት በሆነው ደም ላይ ያስነካዋል። ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ከዚያም ካህኑ በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል።