መጽሐፈ ኢዮብ 16:1-21

መጽሐፈ ኢዮብ 16:1-21 መቅካእኤ

ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እንደዚህ ያለ ነገር አብዝቼ ሰማሁ፥ እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ። በውኑ ከንቱ ቃል መጨረሻ የለውምን? ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድነው? እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፥ ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥ እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር። በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፥ የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር።” “እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፥ ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም። አሁን ግን አድክሞኛል፥ ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል። መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፥ ክሳቴም ተነሥቶብኛል፥ በፊቴም ይመሰክርብኛል። በቁጣው ቆራረጠኝ፥ እርሱም ጠላኝ፥ ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፥ ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፥ እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፥ እያላገጡ ጉንጬን ጠፈጠፉኝ፥ በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ። እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥ በክፋዎችም እጅ ጣለኝ። በርጋታ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፥ አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፥ እንደ ዒላማ አድርጎ አቆመኝ። ቀስተኞቹ ከበቡኝ፥ ኩላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፥ ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ። በቁስል ላይ ቁስል ጨመረብኝ፥ እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል። በቆዳዬ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥ ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ። ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፥ የሞት ጥላ በዐይኖቼ ቆብ ላይ አለ፥ ነገር ግን በእጄ ዓመጽ የለም፥ ጸሎቴም ንጹሕ ነው።” “ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ ለጩኸቴም ማረፊያ አይኑር። አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥ የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው። ወዳጆቼ ናቁኝ፥ ዓይኔም በእግዚአብሔር ፊት እንባ ታፈሳለች። የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ!