መጽሐፈ ኢዮብ 12
12
1ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“በእርግጥም እናንተ የሕዝብ ድምፅ ናችኋ!
ጥበብም ከእናንተ ጋር ትሞታለቻ!
3ነገር ግን እኔም እንደ እናንተ ማስተዋል እችላለሁ፥
ከእናንተም አላንስም፥
እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው?
4ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፥
እግዚአብሔርን የጠራሁ እኔ፥ እርሱም የመለሰልኝ፥
ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል።
5ተደላድሎ የተቀመጠ ሰው መከራን ይንቃል፥
እግሩን ያዳለጠውንም ለመገፍተር ተዘጋጅቶአል።
6የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥
እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዝናንተው ተቀምጠዋል፥
እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል።”#12፥6 “በእጃቸው አምላክን ይጨብጣሉ” ብሎ መተርጎምም ይቻላል። ሐሳቡም አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚቆጣጠሩ እንደሚመስላቸው፥ ነገር ግን በእጃቸው የሚቀረው ጣዖት እንደሚሆን ነው።
7“አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፥
የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8ወይም ለምድር ተናገር፥ እርሷም ታስተምርሃለች፥
የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።
9የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ
ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
10የሕያዋን ሁሉ ነፍስ
የሰውም ሁሉ እስትንፋስ በእጁ ናት።
11ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፥
ጆሮም የቃላትን እውነት ይለይ የለምን?
12ጥበብ በሽምግልና፥
ማስተዋል በረጅም ዕድሜ ይገኛሉ።”
13“በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፥
በእርሱ ዘንድ ምክርና ማስተዋል አለ።
14እነሆ፥ ካፈረሰ፥ የፈረሰው ተመልሶ አይሠራም፥
በሰውም ላይ ከዘጋ፥ ሊከፈት አይችልም።
15እነሆ፥ ውኆቹን ቢከለክል፥ እነርሱ ይደርቃሉ።
እንደገና ቢለቃቸው፥ ምድሪቱን ያጥለቀልቃሉ።
16ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፥
የሚስተውና የሚያስተው የእርሱ ናቸው።
17አማካሪዎችንም እራቁታቸውን ይሰዳቸዋል፥
ፈራጆችንም ሞኝ ያደርጋል።
18የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥
ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል።
19ካህናትን እንደ ምርኮኛ ይወስዳቸዋል፥
ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል።
20ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥
የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል።
21በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥
የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል።
22ከጨለማ ውስጥ ጥልቅን ነገር ይገልጣል፥
የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ይለውጣል።”
23አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፥
አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል።
24ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ያስወግዳል፥
መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል።
25ብርሃንም በሌለበት ጨለማ ይርመሰመሳሉ፥
እንደ ሰካራም ያቅበዘብዛቸዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 12: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ