ትንቢተ ኤርምያስ 7

7
ነቢዩ ኤርምያስ የጌታን ፍርድ መናገሩ
1ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2“በጌታ ቤት በር ቁም፥ ይህንም ቃል በዚያ እንዲህ ብለህ አውጅ፦ ጌታን ልታመልኩ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሰዎች ሆይ! ሁላችሁ የጌታን ቃል ስሙ። 3የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ በዚህም ስፍራ እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ። 4‘የጌታ መቅደስ፥ የጌታ መቅደስ፥ የጌታ መቅደስ ይህ ነው’ እያላችሁ በእነዚህ የሐሰት ቃላት አትታመኑ። 5መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፥ 6መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትጨቊኑ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም እንዳይሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፥ 7ከጥንት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር፥ በዚህ ስፍራ እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ።
8“እነሆ፥ በማይረባ በሐሰት ቃላት ታምናችኋል። 9ትሰርቃላችሁን፥ ትገድላላችሁን፥ ታመነዝራላችሁን፥ በሐሰትም ትምላላችሁን፥ ለበዓልም ታጥናላችሁን፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁን፤ 10መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ፦ እነዚህን አስጸያፊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማድረግ ‘እኛ ድነናል’ አላችሁ። 11#ማቴ. 21፥13፤ ማር. 11፥17፤ ሉቃ. 19፥46።ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ ራሴ አይቻለሁ፥ ይላል ጌታ።”
12 # ኢያ. 18፥1፤ መዝ. 78፥60፤ ኤር. 26፥6። ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደነበረው ስፍራዬ ሂዱ፥ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ምን እንዳደረግሁበት እዩ። 13አሁንም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ ይላል ጌታ፥ በማለዳም ተነሥቼ ባለማቋረጥ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥ 14ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ አደርጋለሁ። 15የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፥ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ።
የሕዝቡ አለመታዘዝ
16“እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው። 17እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን? 18#ኤር. 44፥17-19።እኔን ለማስቆጣት፥ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ፥ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፥ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፥ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ፤ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቁርባን ያፈስሳሉ። 19እኔን ያስቈጣሉን? ይላል ጌታ፤ ለፊታቸውስ እፍረት አይደለምን? 20ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ቁጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይወርዳል፤ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።”
21የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በሌላ መሥዋዕቶቻችሁ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፥ ሥጋውንም ብሉ። 22ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም። 23ነገር ግን፦ “ድምፄን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም እንዲሆንላችሁ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ” ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። 24ነገር ግን በክፉ ልባቸው ሐሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። 25አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ላክሁባችሁ። 26ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ።
27“ይህን ሁሉ ቃላት ለእነርሱ ትናገራለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም።”
28አንተም፦ “የአምላኩን የጌታን ድምፅ ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፤ እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ታጥቶአል። 29ጌታ የቁጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጉርሽን ቁረጪ፥ ጣዪውም፥ በተራቈቱ ኮረብቶችም ላይ ሙሾን አውጪ፥” ትላቸዋለህ። 30“የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፥ ይላል ጌታ፤ ሊያረክሱትም ስሜ በተጠራበትን ቤት ውስጥ ርኩሰታቸውን አኑረዋል። 31#2ነገ. 23፥10፤ ኤር. 32፥35፤ ዘሌ. 18፥21።እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ለማቃጠል፥ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያሉትን የቶፌት መስገጃዎችን ሠረተዋል። 32ስለዚህ፥ እነሆ፥ ስፍራ ከመታጣቱ የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። 33የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራራቸውም የለም። 34#ኤር. 16፥9፤ 25፥10፤ ባሮክ 2፥23፤ ራእ. 18፥23።ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራይቱን ድምፅ አጠፋለሁ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ