ትንቢተ ኤርምያስ 6

6
የወረራው መምጣትና አስፈሪነቱ
1እናንተ የብንያም ልጆች ሆይ! ክፉ ነገር ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ለደህንነታችሁ ሽሹ፥ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፥ በቤትሐካሪም ላይ ምልክት አንሡ። 2የተዋበችውንና የተቀማጠለችውን የጽዮንን ልጅ አጐሳቁላለሁ። 3እረኞችና መንጐቻቸው ወደ እርሷ ይመጣሉ፥ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፥ እያንዳንዱም በስፍራው መንጋውን ያሰማራል። 4“በእርሷ ላይ ጦርነት አዘጋጁ፤ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ።” “ቀኑ መሽቶአልና፥ የማታውም ጥላ ረዝሞአልና ወዮልን!” 5“ተነሡ፥ በሌሊትም እንውጣ፥ የንጉሥ ቅጥሮቿንም እናፍርስ።” 6የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “ዛፎችዋን ቁረጡ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ አፈርን ደልድሉ፤ ይህች ከተማ የምትቀሠፍ ናት፤ በመካከልዋ ያለው ነገር ሁሉ ግፍ ብቻ ነው። 7በጉድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋትዋ ከእርሷ ውስጥ ይፈልቃል፤ ግፍና ቅሚያ በእርሷ መካከል ይሰማል፥ ደዌና ቁስልም ሁልጊዜ በፊቴ አለ። 8ኢየሩሳሌም ሆይ! ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ማንም የማይኖርባት ምድር እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ።”
9የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ሰው ወይኑን እንደሚለቅም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የተረፉትን ፈጽሞ ይለቅሙአችኋል፤ እጅህንም እንደ ለቃሚ በቅርንጫፎቹ ላይ ዳግመኛ ዘርጋ።” 10እንዲሰሙኝስ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘ ነው፥ መስማትም አይችሉም፤ እነሆ፥ የጌታ ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም። 11ስለዚህ በጌታ ቁጣ ተሞልቻለሁ፤ ከመታገሥ ደክሜአለሁ፤ “በጎዳና ባሉ ሕፃናት ላይ በጉልማሶችም ጉባዔ ላይ በአንድነት አፍስሰው፤ ደግሞም ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም በእድሜአቸው ከገፉት ጋር ይያዛሉና። 12እጄን በምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና፤ ቤቶቻቸው እርሻዎቻቸውም ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሆናሉ፥” ይላል ጌታ። 13“ከታናናሾቻቸው ጀምሮ እስከ ታላላቆቻቸ ድረስ ሁሉም በግፍ ለሚገኝ ጥቅም ስስታም ናቸውና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉም ተንኰልን ይፈጽማሉ። 14#ሕዝ. 13፥10።የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፦ ‘ሰላም ሰላም’ ይላሉ። 15#ኤር. 8፥10-12።ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥” ይላል ጌታ።
16ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርሷም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን፦ ‘አንሄድባትም’ አሉ። 17እኔም፦ ‘የመለከቱን ድምፅ አድምጡ’ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን፦ ‘አናደምጥም’ አሉ። 18አሕዛብ ሆይ! ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ! በእነርሱ ምን እንደሚደርስባቸው እወቁ። 19ምድር ሆይ! ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሎቼን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉት፥ በዚህ ሕዝብ ላይ የሐሳባቸውን ፍሬ፥ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ። 20ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር የከበረውንም ዘይት ታመጡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም፥ ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም። 21ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፥ ከዚህ ሕዝብ ፊት ዕንቅፋቶችን አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች በአንድነት ይሰናከሉባቸዋል፥ ጎረቤትና ባልንጀራውም ይጠፋሉ።’ ”
እስራኤልን ጠላት ከሰሜን ይወራታል
22ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን አገር ይመጣል፥ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻዎች ይነሣል። 23ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው፥ ምሕረትንም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኻል፥ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ! ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ።” 24ወሬውን ሰምተናል፥ እጃችን ደክማለች፤ ምጥ ወላድን ሴት እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል። 25የጠላት ሰይፍና ድንጋጤ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ በመንገድም ላይ አትሂዱ። 26የሕዝቤ ሴት ልጅ ሆይ! ማቅ ልበሺ፥ በአመድም ውስጥ ተንከባለዪ፤ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለአንድያ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ፥ መራራ ልቅሶ አልቅሺ።
27“መንገዳቸውን እንድታውቅና እንድትፈትን በሕዝቤ መካከል አቅላጭና ፈታኝ አድርጌሃለሁ። 28እነርሱ ሁሉ እጅግ ዓመፀኞች ናቸው፤ በጠማማነት ይሄዳሉ፤ ናስና ብረት ናቸው፤ ሁሉ ርኩሰትን ያደርጋሉ። 29ወናፉ በኃይል አናፋ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፤ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል ነገረ ግን ኃጢአተኞች አልተወገዱም። 30ጌታ ጥሎአቸዋልና ‘የተጣለ ብር’ ብለው ይጠሩአቸዋል።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ