ትንቢተ ኤርምያስ 5

5
የጌታ ሕዝብ ፍጹም የሆነ ኃጢአት
1በኢየሩሳሌም መንገድ እየተመላለሳችሁ ሩጡ፥ ተመልከቱም፥ እወቁም፥ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደሆነ ይቅር እላታለሁ። 2እነርሱም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ!” ቢሉም እንኳ የሚምሉት በሐሰት ነው። 3አቤቱ! ዓይንህ እውነትን የምትመለከት አይደለችምን? አንተ ቀሥፈሃቸዋል ነገር ግን አላዘኑም፥ ቀጥቅጠሃቸዋልም ነገር ግን ተግሣጽን ለመቀበል እንቢ አሉ፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠንክረዋል፤ ለመመለስ እንቢ አሉ።
4እኔም፦ “የጌታን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና እነዚህ ተሞኝተው ይህን አድርገዋል በእውነት ድሆች ናቸው፤ 5ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ እነርሱንም አናግራቸዋለሁ፤ የጌታን መንገንድና የአምላካቸውን ሕግ ያውቃሉና” አልሁ። እነዚህ ግን ቀንበሩን በአንድነት ሰብረዋል፥ እስራቱንም ቈርጠዋል። 6ስለዚህ ኃጢአታቸው በዝቶአልና፥ የከዳተኝነታቸውም ብዛት ጸንቶአልና ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰብራቸዋል፥ የበረሀም ተኩላ ያጠፋቸዋል፥ ነብርም በከተሞቻቸው ላይ ነቅቶ ይጠብቃል፥ ከዚያም የሚወጣ ሁሉ ይነጠቃል።
7“በእነዚህ ነገሮች ይቅር የምልሽ እንዴት አድርጌ ነው? ልጆችሽ ትተውኛል፥ አማልክትም ባልሆኑ ምለዋል፤ ካጠገብኋቸውም በኋላ አመነዘሩ በጋለሞቶቹም ቤት ተሰበሰቡ። 8እንደ ተቀለቡ ምኞትም እንዳላቸው ፈረሶች ሆኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ኋላ አሽካኩ። 9በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል ጌታ፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
10“በወይኗ ትልሞች በመካከል ሂዱና አበላሹ፥ ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉ፤ የጌታ አይደሉምና ቅርንጫፍዋን ውሰዱ። 11የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በእኔ ላይ እጅግ አታለዋል ይላል ጌታ።
12“እነርሱም፦ ‘ምንም አያደርግም፤ ክፉ ነገርም አይመጣብንም፥ ሰይፍንና ራብንም አናይም፤ 13ነቢያትም ነፋስ ይሆናሉ፥ ቃሉም በእነርሱ የለም፥ እንዲህም ይደረግባቸዋል’ ብለው ጌታን ክደዋል።”
14ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህን ቃል ተናግራችኋልና እነሆ፥ በአፍህ ውስጥ ቃሌን#5፥14 ቃሎቼን። እሳት፥ ይህንም ሕዝብ እንጨት አደርጋለሁ፥ ትበላቸዋለችም። 15የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ፥ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ጽኑ ጥንታዊ ሕዝብ ነው፥ ቋንቋቸውንም የማታውቀው የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው። 16የፍላጻቸውም ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ ሁሉም ኃያላን ናቸው። 17መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፤ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፤ ወይንህንና በለስህንም ይበላሉ፤ የምትተማመንባቸውን የተመሸጉ ከተሞችን በሰይፍ ይደመስሳሉ። 18ነገር ግን በዚያ ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ ፈጽሜ አላጠፋችሁም።”
19እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ፦ “አምላካችን ጌታ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለምን አደረገብን?” ቢሉ፥ አንተ፦ “እንደ ተዋችሁኝ፥ በአገራችሁም ሌሎችን አማልክት እንዳገለገላችሁ፥ እንዲሁ ለእናንተ ባልሆነ አገር ለሌሎች ሰዎች ታገለግላላችሁ” ትላቸዋለህ።
20ይህን በያዕቆብ ቤት አውሩ፥ በይሁዳም አሰሙ፦ 21#ኢሳ. 6፥9፤10፤ ሕዝ. 12፥2፤ ማር. 8፥18።እናንተ ሰነፎችና ልበ ቢሶች፥ ዐይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ! ይህን ስሙ። 22#ኢዮብ 38፥8-11።በውኑ እኔን አትፈሩምን? ይላል ጌታ፤ ከፊቴስ አትደነግጡምን? አልፎት እንዳይሻገር አሸዋን በዘለዓለም ትእዛዝ ለባሕር ድንበር አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፈውም። 23ይህ ሕዝብ ግን እልኸኛና ዐመፀኛ ልብ አለው፤ ዐምፀዋል ሄደዋልም። 24በልባቸውም፦ “የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን ጌታን እንፍራ” አላሉም። 25በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች፥ ኃጢአታችሁም መልካምን ነገር ከለከለቻችሁ።
26በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ እንደ ወፍ አጥማጆችም ያደባሉ፥ ወጥመድንም ይዘረጋሉ ሰዎችንም ያጠምዳሉ። 27ወፍ እንደሞላበት የወፍ ቀፎ፥ እንዲሁ ቤቶቻቸው በሽንገላ ተሞልቶአል፤ ስለዚህም ከብረዋል ባለ ጠጎችም ሆነዋል። 28ወፍረዋል ሰብተዋልም፥ ክፋታቸውንም ያለ ልክ አብዝተዋል፤ የድሀ አደጎች ነገር መልካም እንዲሆንላቸው አልተምዋገቱላቸውም፥ የችግርተኞችንም ፍርድ አልፈረዱላቸውም። 29በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል ጌታ፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
30አሠቃቂና አስደንጋጭ ነገር በምድሪቱ ላይ ሆኖአል፤ 31ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ወድደዋል፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ