ትንቢተ ኤርምያስ 8
8
1“በዚያን ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ የይሁዳን ነገሥታት አጥንትና የመኳንንቶቿን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብራቸው ያወጣሉ። 2በወደዱአቸውና ባገለገሉአቸው፥ በተከተሉአቸውና በፈለጉአቸው፥ በሰገዱላቸውም በፀሐይና በጨረቃ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጉአቸዋል፤ አይሰበሰቡም አይቀበሩምም፥ በምድርም ፊት ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ። 3እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩ፥ ከዚህም ክፉ ወገን የቀሩትን ትሩፋን ሁሉ፥ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
የሕዝቡ እልኸኛ መሆን
4“እንዲህም ትላቸዋለህ፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን? 5እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን አጥብቀው ይዘዋል፥ ለመመለስም እንቢ ብለዋል። 6አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ አንድም ሰው፦ ‘ምን አድርጌአለሁ?’ ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ጦርነትም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል። 7እንዲሁም ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፤ ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመምጫቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የጌታን ፍርድ አላወቁም።
8“እናንተስ፦ ‘ጥበበኞች ነን የጌታንም ሕግ ከእኛ ጋር ነው’ እንዴት ትላላችሁ? እነሆ፥ በውኑ የጸሐፊዎች ሐሰተኛ ብዕር ሐሰት አድርጎታል። 9ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠዋል ተማርከዋልም፤ እነሆ፥ የጌታን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው? 10ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉም በግፍ ለሚገኝ ጥቅም ስስታም ነውና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉም በተንኰል ያደርጋሉና ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ። 11#ሕዝ. 13፥10።የሕዝቤንም ሴት ልጅ ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፦ ‘ስለም ሰላም’ ይላሉ። 12#ኤር. 6፥12-15።አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል ጌታ።”
13ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በወይን ላይ ፍሬ፥ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ አይሆንም፥ ቅጠልም ይረግፋል፤ የሰጠኋቸሁም ይጠፋባቸዋል።
14ዝም ብለን ለምን እንቀመጣለን? ጌታን ስለ በደልን አምላካችን ጌታ አጥፍቶናልና፥ የሐሞትንም ውኃ አጠጥቶናልና ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንግባ በዚያም እንጥፋ። 15ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ መፈወስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ። 16“የፈረሶቻቸው ድምፅ ከዳን ተሰማ፤ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፤ መጡም ምድሪቱንና በእርሷም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። 17እነሆ፥ መርዛቸውን አስማት የማያረክሰው እባቦችንና እፉኝቶችን በእናንተ መካከል እልካለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል፥” ይላል ጌታ።
ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ለወገኑ ማዘኑ
18ኀዘኔ የማይጽናና ነው፥ ልቤም በውስጤ ደክሞአል። 19እነሆ፦ “ጌታ በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርሷ መካከል የለምን?” የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ አገር ተሰማ። “በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድነው?” 20“መከሩ አልፎአል፥ በጋው ተፈጽሟል፥ እኛም አልዳንም።” 21በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ ጠቁሬአለሁም፤ ፍርሀትም ይዞኛል። 22በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለምን አልሆነም?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 8: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ