ትንቢተ ኤርምያስ 49

49
በአሞን ልጆች ላይ የተደረገ ፍርድ
1 # ሕዝ. 21፥28-32፤ 25፥1-7፤ አሞጽ 1፥13-15፤ ሶፎ. 2፥8-11። ስለ አሞን ልጆች፤ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለእስራኤል ልጆች የሉትምን? ወይስ ወራሽ የለውምን? ታዲያ ሚልኮምስ ጋድን ለምን ወረሰ? ሕዝቡስ በከተሞቹ ላይ ለምን ተቀመጠ? 2ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአሞን ልጆች ከተማ በረባት ላይ የጦርነት ውካታን የማሰማበት ቀኖች ይመጣሉ፥ ይላል ጌታ፤ የፍርስራሽ ክምርም ትሆናለች፥ ሴቶች ልጆችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፥ እስራኤልም የወረሱትን ይወርሳል፥ ይላል ጌታ። 3ሐሴቦን ሆይ! ጋይ ፈርሳለችና አልቅሺ፤ እናንተም የረባት ሴቶች ልጆች ሆይ! ሚልኮም ካህናቱና አለቆቹም በአንድነት ይማረካሉና ጩኹ፥ ማቅም ታጠቁ፥ አልቅሱም፥ በቅጥሮችም መካከል ተርዋርዋጡ። 4ማን በእኔ ላይ ይመጣብኛል ብለሽ በመዝገብሽ የታመንሽ አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! በሸለቆችሽ፥ ውኃ በሚፈስስባቸው ሸለቆችሽ፥ ለምን ትመኪያለሽ? 5እነሆ፥ በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ በአንቺ ላይ ፍርሃትን አመጣብሻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እያንዳንዳችሁም በፊታችሁ ወዳለው ስፍራ ትሰደዳላችሁ፥ የሚሸሹትንም የሚሰበስብ የለም። 6“ነገር ግን ከዚያ በኋላ የአሞንን ልጆች ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ።”
በኤዶምያስ ላይ የተደረገ ፍርድ
7 # ኢሳ. 34፥5-17፤ 63፥1-6፤ ሕዝ. 25፥12-14፤ 35፥1-15፤ አሞጽ 1፥11፤12፤ አብ. 1፥1-14፤ ሚል. 1፥2-5። # ባሮክ 3፥22፤23። ስለ ኤዶምያስ፤ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በውኑ በቴማን ጥበብ የለምን? ከብልሃተኞችስ ምክር ጠፍቶአልን? ጥበባቸውስ አልቆአልን? 8የዔሳውን ጥፋት እርሱን በምጐበኝበት ጊዜ አመጣበታለሁና፥ እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ! ሽሹ፥ ወደ ኋላ ተመለሱ፥ በጥልቅም ውስጥ ተቀመጡ። 9ወይን ለቃሚዎች ቢመጡብህ፥ ቃርሚያውን አይተዉልህምን? ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፥ የሚዘርፉት የሚበቃቸውን ያህል አይደለምን? 10እኔ ግን ዔሳውን ዐራቈትሁት፥ የመሸሸጊያውንም ስፍራዎች ገለጥሁ፥ እርሱም ለመሸሸግ አይችልም፤ ዘሩም ወንድሞቹም ጎረቤቶቹም ጠፍተዋል እርሱም የለም። 11ድሀ አደጎችህን ተዋቸው እኔ በሕይወት አኖራቸዋለሁ፤ መበለቶችህም በእኔ ይታመኑ።” 12ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆ፥ ጽዋውን መጠጣት የማይገባቸው ሰዎች ጠጥተውታል፤ አንተስ ሳትቀጣ ፈጽሞ ትቀራለህን? በእርግጥ ትጠጣለህ እንጂ ያለ ቅጣት አትቀርም። 13ባሶራ መሣቀቅያና መሰደቢያ፥ ባድማና መረገሚያ እንድትሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ከተሞችዋም ሁሉ ለዘለዓለም ባድማ ይሆናሉ።”
14ከጌታ ዘንድ መልእክት ሰምቻለሁ በአሕዛብም መካከል፦ “ተሰብሰቡ፥ በእርሷም ላይ ኑ ለጦርነትም ተነሡ” የሚል መልእክተኛ ተልኮአል። 15እነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ታናሽ፥ በሰዎችም መካከል የተናቅህ አድርጌሃለሁ። 16በዓለት ንቃቃት ውስጥ የምትቀመጥ፥ የተራራውን ከፍታ የምትይዝ ሆይ! ማሣቀቅያህና የልብህ ኩራት አታልለውሃል። ምንም እንኳ ጎጆህን እንደ ንስር ጎጆ ከፍ ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል ጌታ። 17“ኤዶምያስም መሣቀቂያ ትሆናለች፥ የሚያልፍባትም ሁሉ ይሣቀቃል፥ ስለ ተደረገባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጭባታል። 18#ዘፍ. 19፥24፤25።ሰዶምና ገሞራ በእነርሱም አጠገብ የነበሩት ጎረቤቶቻቸው እንደ ተገለባበጡ፥ ይላል ጌታ፥ እንዲሁ ማንም ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰው ልጅም አይኖርባትም። 19#ጥበ. 12፥12።እነሆ፥ በጽኑ የበጎች በረት ላይ ከዮርዳኖስ ዱር ውስጥ እንደሚወጣ አንበሳ እንዲሁ እኔ ከእርሷ ዘንድ በድንገት አባርረዋለሁ፤ የተመረጠውንም ማንኛውንም ሰው በእርሷ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ እኔን እንድመጣ የሚጠራኝ ማን ነው? ወይስ በፊቴ የሚቆም እረኛ ማን ነው? 20ስለዚህ ጌታ በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፥ በቴማንም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋው ትንንሾች እንኳ ይጐትቷቸዋል፤ በእውነት የማደሪያቸውም በረት በእነርሱ ላይ ይሣቀቃል። 21ከመውደቃቸው ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ የጩኸትም ድምፅ በኤርትራ ባሕር ተሰማ። 22እነሆ፥ እንደ ንስር ወጥቶ ይበራል ክንፉንም በባሶራ ላይ ይዘረጋል፥ በዚያም ቀን የኤዶምያስ ኃያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል።”
በደማስቆ ላይ የተደረገ ፍርድ
23 # ኢሳ. 17፥1-3፤ አሞጽ 1፥3-5፤ ዘካ. 9፥1። ስለ ደማስቆ፤ ክፉ ወሬ ሰምተዋልና ሐማትና አርፋድ አፈሩ ቀለጡም፤ ለማረፍም እንደማይችል ባሕር በፍርሃት ተናወጡ። 24ደማስቆ ደከመች ለመሸሽም ዘወር አለች መንቀጥቀጥም ያዛት፥ እንደ ወላድም ሴት ጣርና ምጥ ያዛት። 25የተመሰገነችው ከተማ፥ የደስታዬ ከተማ፥ ሳትለቀቅ እንዴት ቀረች? 26ስለዚህ ጐልማሶችዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ወታደሮችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 27በደማስቆም ቅጥር ላይ እሳት አነድዳለሁ የወልደ አዴርንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።
በቄዳርና በአሦር ላይ የተደረገ ፍርድ
28የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ድል ስላደረጋቸው ስለ ቄዳርና ስለ አሦር መንግሥታት፤ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ተነሡ ወደ ቄዳርም ውጡ፥ የምሥራቅንም ልጆች አጥፉ። 29ድንኳኖቻቸውንና መንጋቸውን፥ መጋረጃዎቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን ሁሉ ይወስዳሉ፤ ግመሎቻቸውንም ለራሳቸው እየነዱ ይወስዳሉ፥ እነርሱም፦ በዙሪያቸው ሁሉ ሽብር አለ፥ እያሉ ለእነርሱ ይጮኻሉ። 30እናንተ በአሦር የምትኖሩ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ተማክሮባችኋልና፥ አሳብም አስቦባችኋልና ሽሹ ወደ ሩቅም ስፍራ ሂዱ በጥልቁም ውስጥ ተቀመጡ፥ ይላል ጌታ። 31“ተነሡ፥ በደኅንነት ተቀምጦ ተረጋግቶ ወዳለው፥ የቅጥር በርና መቀርቀሪያ ወደሌለው ብቻውንም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ውጡ፥ ይላል ጌታ። 32ግመሎቻቸው ይበዘበዛሉ የእንስሶቻቸውም ብዛት ይማረካል፤ ጠጉራቸውንም ዙሪያውን የተላጩትን ሰዎች ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከሁሉም አቅጣጫ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ። 33አሦርም የቀበሮዎች መኖሪያና የዘለዓለም ባድማ ትሆናለች፤ በዚያም ማንም ሰው አይኖርም፥ የሰው ልጅም አይቀመጥባትም።”
በኤላም ላይ የተደረገ ፍርድ
34በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ስለ ኤላም ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። 35የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ዋና የኃይላቸው መሣሪያ የሆነውን የኤላምን ቀስት እሰብራለሁ። 36ከአራቱም ከሰማይ ማዕዘናት አራቱን ነፋሳት በኤላም ላይ አመጣለሁ፥ ወደ እነዚያም ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከኤላም የተሰደዱ ሰዎች ተሰድደው ያልደረሱበት ሕዝብ አይገኝም። 37በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን በሚሹአት ፊት ኤላምን አስደነግጣለሁ፤ በእነርሱም ላይ ጽኑ ቁጣዬ የሆነውን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በኋላቸው ሰይፍ እልክባቸዋለሁ፤ 38ዙፋኔንም በኤላም አኖራለሁ ከዚያም ንጉሡንና ሹማምንትን አጠፋለሁ፥ ይላል ጌታ። 39ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የኤላምን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ