ትንቢተ ኤርምያስ 48
48
በሞዓብ ላይ የተደረገ ፍርድ
1 #
ኢሳ. 15፥1—16፥14፤ 25፥10-12፤ ሕዝ. 25፥8-11፤ አሞጽ 2፥1-3፤ ሶፎ. 2፥8-11። ስለ ሞዓብ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ናባው ጠፍታለችና ወዮላት! ቂርያታይም አፍራለች ተይዛለችም፤ አምባይቱም አፍራለች ፈርሳለችም። 2ከእንግዲህ ወዲህ የሞዓብ ትምክሕት የለም፤ በሐሴቦን ሆነው፦ ኑ ሕዝብ እንዳትሆን እናጥፋት፥ ብለው ክፉ ነገር አስበውባታል። መድሜን ሆይ! አንቺ ደግሞ በጸጥታ ትዋጫለሽ ሰይፍም ያሳድድሻል። 3መፍረስና ታላቅ ጥፋት፥ የሚል የጩኸት ድምፅ ከሖሮናይም ተሰማ። 4ሞዓብ ጠፍታለች፥ ልጆችዋም ጩኸትን አሰምተዋል። 5በሉሒት አቀበት መራር ልቅሶ እያለቀሱ ይወጣሉና፥ በሖሮናይምም ቁልቁለት የጥፋትንና የጣርን ጩኸት ሰምተዋል። 6ሸሽታችሁ ራሳችሁን አድኑ፤ በምድረ በዳ እንዳለ ቁጥቋጦ#48፥6 ይህን ቃል “የሜዳ አህያ” ብለው የሚተረጉሙ ቅጂዎች አሉ። ሁኑ። 7በሥራሽና በመዝገብሽ ታምነሻልና አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል። 8ጌታም እንደ ተናገረው፥ አጥፊው ወደ ከተማ ሁሉ ይመጣል አንዲትም ከተማ አትድንም፤ ሸለቆውም ይጠፋል ሜዳውም እንዳልነበረ ይሆናል። 9በርራ እንድትወጣ ለሞዓብ ክንፍ ስጡአት፤ ከተሞችዋም ሰው የማይኖርባቸው ባድማ ይሆናሉ። 10የጌታን ሥራ በቸልታ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፥ ደም ከማፍሰስም ሰይፉን የሚከለክል ርጉም ይሁን።
11ሞዓብ ከብላቴንነቱ ጀምሮ ተረጋግቷል፥ በአምቡላውም ላይ ዐርፎአል፥ ከዕቃም ወደ ዕቃ አልተንቈረቈረም፥ ወደ ምርኮም አልሄደም፤ ስለዚህ ቃናው በእርሱ ውስጥ ቀርቶአል፥ መዓዛውም አልተለወጠም። 12ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሚያገላብጡትን የምልክበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፥ እነርሱም ያገላብጡታል፤ ጋኖቹንም ባዶ ያደርጋሉ፥ መስቴዎቹንም ይሰብራሉ። 13የእስራኤልም ቤት መተማመኛቸው በነበረችው በቤቴል እንዳፈረ፥ እንዲሁ ሞዓብ በካሞሽ ያፍራል። 14እናንተ፦ እኛ ኃያላን በውጊያም ጽኑዓን ነን፥ እንዴት ትላላችሁ? 15ወደ ሞአብና ከተሞችዋ አጥፊው ወጥቶአል፥ የተመረጡትም ጉልማሶች ወደ መታረድ ወርደዋል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የሆነ ንጉሥ። 16የሞዓብ ጥፋት ለመምጣት ቀርቦአል የእርሱም መከራ እጅግ ፈጥኖአል። 17በዙሪያው ያላችሁ ሁሉ ስሙንም የምታውቁ ሁሉ፦ ብርቱው በትረ መንግሥት፥ የከበረው ሽመል፥ እንዴት ተሰበረ!፥ ብላችሁ አልቅሱለት። 18በዲቦን የምትኖሪ ሆይ! ሞዓብን የሚያጠፋ ወጥቶብሻልና፥ አምባሽንም ሰብሮአልና ከክብርሽ ውረጂ በደረቅም መሬት ላይ ተቀመጪ። 19በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ! በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤ የሸሸውንና ያመለጠችውን፦ ምን ሆኖአል?፥ ብለሽ ጠይቂ። 20ሞዓብም ፈርሶአልና አፈረ፤ አልቅሱ ጩኹም፤ ሞዓብ እንደ ጠፋ በአርኖን አጠገብ አውጁ። 21ፍርድም በሜዳው ላይ፥ በሖሎን፥ በያሳ፥ በሜፍዓት ላይ፥ 22በዲቦን፥ በናባው፥ በቤት ዲብላታይም ላይ፥ 23በቂርያታይም፥ በቤትጋሙል፥ በቤትምዖን ላይ፥ 24በቂርዮት፥ በባሶራ፥ በሞዓብም ምድር በቅርብና በሩቅ ባሉ ከተሞች ሁሉ ላይ መጥቷል። 25የሞዓብ ቀንድ ተቈረጠ ክንዱም ተሰበረ፥ ይላል ጌታ።
26በጌታ ላይ ኰርቶአልና አስክሩት፤ ሞዓብም በጥፋቱ ላይ ይንከባለላል፥ ደግሞም መሳቂያ ይሆናል። 27ለአንተ እስራኤል መሳቂያ አልነበረምን? ወይስ ስለ እርሱ በተናገርህ ቊጥር ራስህን የምትነቀንቀው በሌቦች መካከል ተገኝቶአልን?። 28እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ! ከተሞችን ትታችሁ በዓለት ንቃቃት መካከል ተቀመጡ፥ በገደል አፋፍም ቤትዋን እንደምትሠራ እንደ ርግብ ሁኑ። 29እጅግ እንደ ታበየ ስለ ሞዓብ ትዕቢት ስለ ትምክህቱም ስለ ኩራቱም ስለ እብሪቱም ስለ ልቡም ትዕቢት ሰምተናል። 30እኔ እብሪቱን አውቃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ፉከራው ሐሰት ነው፥ ሥራውም ሐሰት ነው። 31ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ ለሞዓብም ሁሉ እጮኻለሁ፤ ለቂርሔሬስ ሰዎች አለቅሳለሁ። 32አንቺ የሴባማ ወይን ሆይ! ከኢያዜር ልቅሶ ይልቅ ለአንቺ አለቅሳለሁ፤ ቅርንጫፎችሽ ባሕርን ተሻግረዋል፥ ወደ ኢያዜርም ባሕር ደርሰዋል፤ አጥፊው በበጋ ፍሬሽና በወይንሽ ላይ መጥቷል። 33ሐሤትና ደስታ ከፍሬያማው እርሻና ከሞዓብ ምድር ጠፍተዋል፤ የወይ ጠጁን ከወይን መጥመቂያው አጥፍቻለሁ፤ ጠማቂውም በእልልታ አይጠምቅም፥ እልልታቸውም እልልታ አይሆንም። 34ከሐሴቦን ጮኹ እስከ ኤልያሊና እስከ ያሀጽ ድረስ ድምፃቸውን አሰሙ፤ ከዞዓር እስከ ሖሮናይምና እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ደርሶአል፤ የኔምሬም ውኃ ደግሞ ይደርቃል። 35በኮረብታው መስገጃ ላይ የሚሠዋውን ለአማልክቱም የሚያጥነውን ከሞዓብ አጠፋለሁ፥ ይላል ጌታ።
36ያተረፈው ትርፉ ጠፍቶበታልና፤ ስለዚህ ልቤ ለሞዓብ እንደ እንቢልታ ድምፅ ይቃትታል፥ ልቤም ለቂርሔሬስ ሰዎች እንደ እንቢልታ ድምፅ ይቃትታል። 37“ራስ ሁሉ መላጣ ጢምም ሁሉ የተላጨ ነውና፤ በእጅም ሁሉ ላይ መተልተል በወገብም ላይ ማቅ አለና። 38ሞዓብን ማንም እንደማይፈልገው ዕቃ ሰብሬዋለሁና በሞዓብ ሰገነት ሁሉ ላይ በአደባባዩም ላይ በሁሉም ቦታ ልቅሶ አለ፥ ይላል ጌታ። 39እንዴት ተሰበረ! እንዴትስ አለቀሱ! በእፍረትም የተነሣ ሞዓብ ጀርባውን እንዴት ሰጠ! ስለዚህ ሞዓብ በዙሪያው ላሉት ሁሉ መሳቂያና መደንገጫ ሆኖአል።”
40ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ እንደ ንስር ይበርራል ክንፉንም በሞዓብ ላይ ይዘረጋል። 41ከተሞቹ ተይዘዋል፥ አምባዎቹም ተወስደዋል፥ በዚያም ቀን የሞዓብ ኃያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ሆኖአል። 42ሞዓብም በጌታ ላይ ኰርቶአልና ከእንግዲህ ወድያ ሕዝብ አይሆንም፥ እርሱም ይጠፋል። 43በሞዓብ የምትኖር ሆይ! ፍርሃትና ጉድጓድ ወጥመድም በአንተ ላይ አለ፥ ይላል ጌታ። 44በሞዓብ ላይ የመጐብኘትን ዓመት አመጣበታለሁና፥ ይላል ጌታ፤ ከአስፈሪውም ነገር የሸሸ በጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፥ ከጉድጓድም ውስጥ የሚወጣ በወጥመድ ይያዛል። 45“የሸሹ ደክመው ከሐሴቦን ጥላ በታች ቆመዋል፤ እሳት ከሐሴቦን ነበልባልም ከሴዎን መካከል ወጥቶአል የሞዓብን ግንባር የሁከትንም ልጆች ዘውድ በልቶአል። 46ሞዓብ ሆይ! ወዮልህ! የካሞሽ ሰዎች ጠፍቶአል፤ ወንዶች ልጆችህ ተማርከዋልና፥ ሴቶች ልጆችህም ወደ ምርኮ ሄደዋልና። 47ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ።” የሞዓብ ፍርድ እስከዚህ ድረስ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 48: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ