ትንቢተ ኤርምያስ 50

50
በባቢሎን ላይ የተደረገ ፍርድ
1 # ኢሳ. 13፥1—14፥23፤ 47፥1-15። ጌታ ስለ ከለዳውያን ምድር ስለ ባቢሎን በነቢዩ በኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2በአሕዛብ መካከል ተናገሩ አውጁም፥ ዓላማውንም አንሡ፤ አውጁ፥ ሳትደብቁም እንዲህ በሉ፦ ባቢሎን ተያዘች፥ ቤል አፈረ፥ ሜሮዳክ ተሰባበረ፤ ምስሎችዋ አፈሩ፥ ጣዖታትዋ ተሰባበሩ። 3ሕዝብ ከሰሜን በእርሷ ላይ ወጥቶባታል ምድርዋንም ባድማ ያደርጋል፥ የሚቀመጥባትም አይገኝም፤ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል። 4በዚያም ወራት በዚያም ጊዜ፥ ይላል ጌታ፥ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው ይመጣሉ፥ እያለቀሱም መንገዳቸውን ይሄዳሉ፥ አምላካቸውንም ጌታን ይፈልጋሉ። 5ፊታቸውንም ወደዚያ አቅንተው፦ ኑ፥ ከቶ በማይረሳ በዘለዓለም ቃል ኪዳን ከጌታ ጋር በአንድነት እንሁን፥ ብለው ወደ ጽዮን የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ።
6ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤ እረኞቻቸው አሳቱአቸው፥ ከተራሮችም ላይ እንዲያፈገፍጉ አደረጉአቸው፤ ከተራራ ወደ ኮረብታ ሄደዋል፥ በረታቸውንም ረስተዋል። 7ያገኙአቸው ሁሉ አጠፉአቸው፥ ጠላቶቻቸውም፦ በጽድቅ ማደሪያ በጌታ ላይ፥ በአባቶቻቸው ተስፋ በጌታ ላይ እነርሱ ኃጢአት ስለ ሠሩ እኛ አልበደልንም፥ አሉ። 8#ራእ. 18፥4።ከባቢሎን መካከል ሽሹ፥ ከከለዳውያንም ምድር ውጡ፥ በመንጎችም ፊት እንደ አውራ ፍየሎች ሁኑ። 9እነሆ፥ ከሰሜን ምድር የታላላቅ አሕዛብን ጉባኤ አስነሣለሁ በባቢሎንም ላይ አመጣቸዋለሁ፤ በእርሷም ላይ ይሰለፋሉ፥ ከዚያም ትያዛለች፤ ፍላጾቻቸውም ተጨናግፎ ባዶውን እንደማይመለስ እንደ ብልህ ጀግና ፍላጻ ናቸው። 10የከላውዴዎንም ምድር ትበዘበዛለች፥ የሚበዘብዙአትም ሁሉ ይጠግባሉ፥ ይላል ጌታ።
11ርስቴን የምትበዘብዙ እናንተ ሆይ! ደስ ቢላችሁ፥ ሐሤትንም ብታደርጉ፥ በማበራየት ላይም እንዳለች ጊደር ብትፈነጩ፥ እንደ ብርቱዎችም ፈረሶች ብታሽካኩ እንኳ፥ 12እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፥ የወለደቻችሁም ትዋረዳለች፤ እነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ኋለኛይቱ ትሆናለች፤ ምድረ በዳና ደረቅ ምድር በረሀም ትሆናለች። 13ከጌታ ቁጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ ሰው አይቀመጥባትም፤ በባቢሎንም በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይሣቀቃል በመጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጫል። 14እናንተ ቀስትን የምትገትሩ ሰዎች ሁሉ፥ ባቢሎንን ዙሪያዋን ክበቡ፤ በጌታ ላይ ኃጢአት ሠርታለችና ወርውሩባት ፍላጻንም አታስቀሩ። 15የጌታ በቀል ነውና በዙሪያዋ ሆናችሁ በእርሷ ላይ ጩኹ፤ እጅዋን ሰጠች፤ ግንቦችዋ ወደቁ ቅጥሮችዋም ፈረሱ፤ እርሷን ተበቀሉ እንደ ሠራችውም ሥሩባት። 16ዘሪውንና በመከር ጊዜ ማጭድ የሚይዘውን ከባቢሎን አጥፉ፤ የአስጨናቂው ሰው ከሆነው ሰይፍ ፊት እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።
17እስራኤል የባዘነ በግ ነው፤ አንበሶች አሳደዱት፤ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፥ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አጥንቱን ቈረጠመው። 18ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ። 19እስራኤልንም ወደ ማሰማርያው እመልሳለሁ፥ በቀርሜሎስና በባሳንም ላይ ይሰማራል፥ ሆዱም በኤፍሬም ተራራና በገለዓድ ላይ ትጠግባለች። 20እንደትሩፍ የተውኳቸውን እነዚያን ይቅር እላቸዋለሁና በዚያን ወራት በዚያም ዘመን፥ ይላል ጌታ፥ የእስራኤል በደል የይሁዳም ኃጢአት ይፈለጋል ነገር ግን በዚያ ምንም አይገኝም።
21በምራታይም ምድር ላይ በፋቁድም በሚኖሩት ላይ ውጣ፤ ግደላቸው ፈጽመህም አጥፋቸው፥ ይላል ጌታ፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ አድርግ። 22የጦርነት ሁካታ ታላቅም ጥፋት በምድሪቱ ላይ አለ። 23የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ደቀቀ እንዴትስ ተሰበረ! ባቢሎንስ በአሕዛብ መካከል እንዴት መሣቀቅያ ሆነች! 24ባቢሎን ሆይ! አጥምጄብሻለሁ አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤ ከጌታ ጋር ስለ ታገልሽ#50፥24 ስለ ተሟገትሽ ተገኝተሻል ተይዘሻልም። 25የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር የሚፈጽመው ሥራ አለውና ጌታ የጦር ግምጃ ቤቱን ከፍቶ የቁጣውን የጦር መሣርያ አወጣ። 26ከየአቅጣጫው በእርሷ ላይ ኑ፥ ጎተራዎችዋንም ክፈቱ፤ እንደ ተቈለለ ነዶ ከምርዋት ፈጽማችሁም አጥፉአት፥ ምንም ዓይነት ነገር አታስተርፉላት። 27ወይፈኖችዋን ሁሉ እረዱ፥ ወደ መታረድም ይውረዱ፤ ቀናቸው፥ የመጐብኘታቸው ጊዜ ደርሶአልና ወዮላቸው! 28የአምላካችንን የጌታን በቀል ስለ መቅደሱም ሲል የሚበቀለውን በቀል በጽዮን ለመናገር ከባቢሎን ምድር የሚመጡትን የኰብላዮችና የስደተኞች ድምፅ አድምጡ።
29 # ራእ. 18፥6። ቀስትን የሚገትሩትን ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩአቸው፤ በዙሪያዋ ስፈሩባት አንድም ሰው አያምልጥ፤ በእስራኤል ቅዱስ በጌታ ላይ በኩራት አልታዘዝም ብላለችና እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፥ እንዳደረገችም ሁሉ አድርጉባት። 30ስለዚህ ጐልማሶችዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ወታደርዎችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ። 31ትዕቢተኛው ሆይ! የመጐብኘትህ ጊዜ፥ ቀንህ ደርሶአልና እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 32ትዕቢተኛው ተሰናክሎ ወድቆአ የሚያነሣውም ማንም የለም፤ በከተሞቹም ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፥ በዙሪያውም ያለውን ሁሉ ትበላለች።
33የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተጨቊነዋል፥ የማረኳቸውም ሁሉ በኃይል ይዘዋቸዋል፥ እነርሱንም ለመልቀቅ እንቢ ብለዋል። 34የሚዋጃቸው ብርቱ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ ነው፤ ምድሪቱንም ለማሳረፍ በባቢሎንም የሚኖሩትን ለማወክ ሙግታቸውን ፈጽሞ ይሟገታል። 35ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ፥ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፥ ይላል ጌታ። 36ሰይፍ በምዋርተኞች ላይ አለ ሞኞችም ይሆናሉ፥ ሰይፍም በኃያላኖችዋ ላይ አለ እነርሱም ይጠፋሉ። 37ሰይፍ በፈረሶችዋና በሰረገሎችዋ ላይ በመካከልዋም ባሉት በባዕድ ሕዝብ ሁሉ ላይ አለ፥ እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ፤ ሰይፍም በመዝገቦችዋ ላይ አለ እነርሱም ይበዘበዛሉ። 38እርሷ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናትና፥ እነርሱም በጣዖታቱ ላይ እንደ እብድ ይሆናሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ። 39#ራእ. 18፥2።ስለዚህ በባቢሎን የምድረ በዳ አራዊት ከተኩላዎች ጋር ይቀመጡባታል፥ ሰጐኖችም ይቀመጡባታል፤ ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘለዓለም አይቀመጥባትም፥ እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም። 40#ዘፍ. 19፥24፤25።ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ጎረቤቶቻቸውን እግዚአብሔር እንደ ገለባበጣቸው፥ ይላል ጌታ፥ እንዲሁ ማንም ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰው ልጅም አይኖርባትም።
41እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን ይመጣል፤ ታላቅ ሕዝብና ብዙ ነገሥታትም ከምድር ዳርቻ ይነሣሉ። 42ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው ምሕረትም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር የሚተምም ነው፤ በፈረሶች ላይ ይቀመጣሉ፤ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ! ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ። 43የባቢሎን ንጉሥ ወሬአቸውን ሰምቶአል፥ እጆቹም ደክመዋል፥ ጣርም ይዞታል፥ ምጥ ወላድ ሴትን እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞታል። 44እነሆ፥ በጽኑ የበጎች በረት ላይ ከዮርዳኖስ ዱር ውስጥ እንደሚወጣ አንበሳ እንዲሁ እኔ ከእርሷ ዘንድ በድንገት አባርራቸዋለሁ፤ የተመረጠውንም ማንኛውንም ሰው በእርሷ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ እኔን እንድመጣ የሚጠራኝ ማን ነው? ወይስ በፊቴ የሚቆም እረኛ ማን ነው? 45ስለዚህ ጌታ በባቢሎን ላይ የመከረባትን ምክር፥ በከለዳውያንም ምድር ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋው ትንንሾች እንኳ ይጐትቷቸዋል፤ በእውነት የማደሪያውም በረት በእነርሱ ላይ ይሣቀቃል። 46ባቢሎን ስትያዝ ከነበረው የሁካታ ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ ጩኸትም በአሕዛብ መካከል ተሰማ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ