የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 2

2
እስራኤል ንስሐ እንድትገባ ጌታ መጠየቁ
1የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“ሂድ፥ በኢየሩሳሌም ጆሮዎች ላይ አውጅ፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የብላቴንነትሽን ጽኑ ፍቅር የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስታውሼዋለሁ። 3እስራኤል ለጌታ ቅዱስ ነበረ፥ የአዝመራውም በኵራት ነበረ፤ የበሉት ሁሉ እንደ በደለኞች ይቈጠራሉ፥ ክፉም ነገር ይመጣባቸዋል፥ ይላል ጌታ።”
4የያዕቆብ ቤት የእስራኤልም ቤት ወገኖች ሁሉ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ። 5ጌታ እንዲህ ይላል፦ “አባቶቻችሁ ከእኔ የራቁት፥ ከንቱነትንም የተከተሉት፥ ከንቱም የሆኑት ምን ስሕተት አግኝተውብኝ ነው? 6እነርሱም፦ ‘ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳም በባድማ ጉድጓድም ባለበት ምድር፥ በውኃ ጥምና በሞት ጥላ ምድር፥ ማንም በማያልፍበትና ማንም በማይቀመጥበት ምድር የመራን ጌታ ወዴት አለ?’ አላሉም። 7ፍሬዋንና በረከትዋንም እንድትበሉ ወደ ፍሬያማ ምድር አስገባኋችሁ፤ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ፥ ርስቴንም የተጠላች አደረጋችሁ። 8ካህናቱም፦ ‘ጌታ ወዴት አለ?’ አላሉም፥ የሕግ አዋቂዎች አላወቁኝም፤ ገዢዎችም ዐመፁብኝ፥ ነቢያትም በበዓል ትንቢት ተናገሩ፥ የማይረባውንም ነገር ተከተሉ።
9“ስለዚህ ከእናንተ ጋር ገና እከራከራለሁ፥ ይላል ጌታ፥ ከልጆቻችሁም ልጆች ጋር እከራከራለሁ። 10ወደ ኪቲም ደሴቶች ተሻገሩና ተመልከቱ፥ ወደ ቄዳርም ላኩና በጣም በጥንቃቄ መርምሩ፥ እነሆ እንዲህ ያለ ነገር ሆኖ እንደሆነ እዩ። 11በውኑ አማልክት ያልሆኑትን አማልክቱን የለወጣቸው አንድ ሕዝብ አለን? ነገር ግን ሕዝቤ ክብሩን በማይረባ ነገር ለወጠ። 12ሰማያት ሆይ! በዚህ ተሣቀቁ፥ እጅግም ደንግጡና ተንቀጥቀጡ ይላል ጌታ። 13ሕዝቤ ሁለት ክፉ ነገሮችን ሠርቷል፤ እኔን የሕይወት ውኃ ምንጭን ትተውኛል፥ ውኃ መቋጠር የማይችሉ የተሸነቈሩ ጉድጓዶች ለራሳቸው ቆፍረዋል።
14“በውኑ እስራኤል ባርያ ነውን? ወይስ በቤት የተወለደ አገልጋይ ነውን? ስለምን ለብዝበዛ ሆነ? 15የአንበሳ ደቦሎች በእርሱ ላይ አገሡ፥ ድምፃቸውንም አሰሙ፤ ምድሩንም ባድማ አደረጉ፥ ከተሞቹም ፈርሰዋል የሚቀመጥባቸውም የለም። 16ደግሞም የሜምፎስና የጣፍናስ ልጆች የእራስሽን ዘውድ የሆነውን ፀጉርሽን ይላጩሻል። 17በመንገድ በመራሽ ጊዜ ጌታ አምላክሽን በመተው በራስሽ ላይ ይህን አላመጣሽምን? 18አሁንስ የሺሖርን ውኃ ለመጠጣት ወደ ግብጽ በመሄድሽ የምታገኚው ምን ነገር አለ? የኤፍራጥስንም ውኃ ለመጠጣት ወደ አሦር በመሄድሽ የምታገኚው ምን ነገር አለ? 19ክፋትሽ ይቀጣሻል ክህደትሽ ይገሥጽሻል፤ ጌታን አምላክሽን መተውሽ ምን ያኽል ክፉና መራራ ነገር እንደሆነ እወቂም፥ ተመልከቺም፤ እኔን መፍራት በአንቺ ውስጥ የለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
20“ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰብረሻል እስራትሽንም በጥሰሻል፤ አንቺም፦ ‘አላገለግልም’ አልሽ፥ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ። 21እኔ የተመረጠች ወይን ፍጹምም እውነተኛ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን የተበላሸ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ? 22በእንዶድ ብትታጠቢም፥ ለራስሽም ሳሙናን አብዝተሽ ብትጠቀሚ እንኳ፥ በእኔ ፊት በኃጢአትሽ ረክሰሻል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 23አንቺስ፦ ‘ራሴን አላረከስኩም በዓሊምንም አልተከተልኩም’ እንዴት ትያለሽ? በሸለቆ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ፥ ምን እንዳደረግሽም እወቂ፤ በመንገዶችዋ ላይ ወድያና ወዲህ የምትቅበዘበዥ ወጣት ግመል ሆነሻል፤ 24በምኞትዋ ነፋስን እንደምታሸትት፥ በምድረ በዳ እንደ ለመደች እንደ ሜዳ አህያ ነሽ፤ ከጋለው ምኞትዋ የሚመልሳት ማን ነው? የሚሹአት ሁሉ አይደክሙም፥ በወራትዋ ያገኙአታል። 25በባዶ እግርሽ ከመሄድ፥ ጉሮሮሽንም ከውኃ ጥም ከልክዪ፤ አንቺ ግን፦ ‘ተስፋ የለኝም፥ አይሆንም! እንግዶችን ወድጄአለሁና፥ እከተላቸዋለሁም’ አልሽ።
26“ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር እንዲሁ የእስራኤል ቤት፥ እነርሱና ንጉሦቻቸውም አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነብዮቻቸውም ያፍራሉ። 27ግንዱን፦ ‘አንተ አባቴ ነህ፤’ ድንጋዩንም፦ ‘አንቺ ወለድሺኝ’ ይላሉ፤ ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፥ በመከራቸው ጊዜ ግን፦ ‘ተነሥተህ አድነን’ ይላሉ። 28ለራስህ የሠራሃቸው አማልክትህ ወዴት ናቸው? ይሁዳ ሆይ! አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር ብዛት እንዲሁ ናቸውና እስቲ ይነሡ በመከራህም ጊዜ ያድኑህ።
29“ከእኔ ጋር የምትከራከሩት ለምንድን ነው? ሁላችሁ ዐምፃችሁብኛል ይላል ጌታ። 30ልጆቻችሁን በከንቱ ቀሥፌአቸዋለሁ፤ ተግሣጽን አልተቀበሉም፤ ሰይፋችሁ እንደሚሰባብር አንበሳ ነብዮቻችሁን በልቶአል። 31ትውልድ ሆይ! የጌታን ቃል ተመልከቱ። በውኑ ለእስራኤል ምድረ በዳ ወይስ የጨለመች ምድር ሆንኩባትን? ሕዝቤስ ስለምን፦ ‘እኛ ፈርጥጠናል፤ ዳግመኛ ወደ አንተ አንመጣም’ ይላሉ? 32በውኑ ኰረዳ ጌጥዋን ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጣጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን በቍጥር ለማይቆጠሩ ቀናቶች ረስተውኛል። 33ፍቅርን ለመሻት መንገድሽን እንዴት በጥንቃቄ ታስተካክያለሽ! ስለዚህም ለክፉዎች ሴቶች እንኳ መንገድሽን አስተምረሻል። 34እንዲሁም ሲምሱ አልያዝሻቸውም ነገር ግን በልብሶችሽ ላይ የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቶአል፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ብትፈጽሚም እንኳ 35አንቺ ግን፦ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤ በእውነት ቁጣው ከእኔ ተመልሶአል’ አልሽ። እነሆ፦ ‘ኃጢአት አልሠራሁም’ ብለሻልና በፍርድ እከስሻለሁ። 36መንገድሽን ለመለወጥ ለምን በጣም ትሮጫለሽ? አሦር እንዳሳፈረሽ ግብጽ እንዲሁ ያሳፍርሻል። 37ከዚያ ደግሞ እጆችሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ትወጫለሽ፥ ምክንያቱም ጌታ የታመንሽባቸውን ጥሎአልና፥ በእነርሱም አይከናወንልሽም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ