ትንቢተ ኤርምያስ 10:1-13

ትንቢተ ኤርምያስ 10:1-13 መቅካእኤ

እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ! ጌታ በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የአሕዛብን መንገድ አትማሩ፥ ከሰማይ ምልክቶችም የተነሣ አትፍሩ፤ አሕዛብ ከእነርሱ የተነሣ ይፈራሉና። የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሞያተኛውም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል። በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። በዱባ እርሻ (የአትክልት ስፍራ) ውስጥ እንዳለ እንደ ወፍ ማስፈራርያ ዓምድ ናቸው፥ እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም ስለማይችሉ ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራት አይችሉምና፥ ደግሞም መልካም መሥራት በእነርሱ ውስጥ የለምና አትፍሩአቸው።” ጌታ ሆይ! እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው። የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለ ሌለ፥ አንተን መፍራት ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው? በአንድ ጊዜ ቂላ ቂሎችና ሞኞች ሆነዋል፤ ጣዖታት የሚያስተምሩት ከግዑዝ እንጨት የማይሻልን ነገር ብቻ ነው። የሞያተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፤ ልብሳቸውም ሰማያዊና ሐምራዊ ነው፥ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው። ጌታ ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቁጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን መቋቋም አይችሉም። እናንተም፦ “ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ” ትሉአቸዋላችሁ። ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳርቻ ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል።