የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 66

66
1 # ማቴ. 5፥34፤ 23፥22፤ ማቴ. 5፥35። # የሐዋ. 7፥49-50። ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድነው? 2እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለች፤ እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል ጌታ። ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
3በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቁርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው። እጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኩሰታቸው ደስ ይላታል፤
4እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ። ምክንያቱም በፊቴ ክፉ ነገርን አድርገዋል፥ ያልወደድሁትንም መርጠው በጠራኋቸው ጊዜ አልመለሱልኝም፤ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝም።
5እናንት በቃሉ ፊት የምትርዱ፥ የጌታን ቃል ስሙ፦ የጠሉአችሁ የናንተው ሕዝብ፥ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ፦ “ደስታችሁን እንድናይ ጌታ ይክበር” ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ።
6የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የጌታ ድምፅ ተሰምቶአል።
7 # ራእ. 12፥5። ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያስጭንቃት ወንድ ልጅን ወለደች።
8ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳል? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና።
9በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ እንዳይወለድ አደርጋለሁን? ይላል ጌታ፤ ሊወልድ የተቃረበውን ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ።
10እናንተ የምትወዷት ሁሉ፥ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፤ ስለ እርሷም ደስ ይበላችሁ፤ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፥ ከእርሷ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፤
11እንድትጠቡ ከማጽናናትዋም ጡት እንድትጠግቡ፥ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ እንዲላችሁ።
12ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆም፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ከዚያም ትጠባላችሁ፥ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጉልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሏችኋል።
13እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ።
14ታያላችሁ፥ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፥ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የጌታም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፥ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል።
15እነሆ፥ ጌታ መዓቱን በቁጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ።
16ጌታም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል፤ በጌታም ተወግተው የሞቱት ይበዛሉ።
17በመሀከላቸው ያለውን አንዱን ተከትለው ወደ መናፈሻ ስፍራው ለመግባት ሰውነታቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፥ የእሪያንም ሥጋ፥ አስጸያፊ ነገርንም፥ አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ።
18ሥራቸውንና አሳባቸውን አውቃለሁ፤ አሕዛብንና ልሣናትን ሁሉ የምትሰበስብበት ጊዜ ይደርሳል፤ እነርሱም ይመጣሉ፥ ክብሬንም ያያሉ። 19በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፥ ወደ ፉጥ፥ ወደ ሉድ፥ ወደ ሞሳሕ፥ ወደ ቶቤል፥ ወደ ያዋን፥ በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ።
20የእስራኤል ልጆች ቁርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ ጌታ ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁም ለጌታ ቁርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል ጌታ። 21ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል ጌታ።
22 # ኢሳ. 65፥17፤ 2ጴጥ. 3፥13፤ ራእ. 21፥1። እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል ጌታ። 23እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ለመስገድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል ጌታ። 24#ዮዲ. 16፥17፤ ማር. 9፥48።ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ