ኦሪት ዘፍጥረት 46:1-27

ኦሪት ዘፍጥረት 46:1-27 መቅካእኤ

እስራኤልም ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፥ ወደ ቤርሳቤህ ደረሰ፥ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ። እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ፦ “ያዕቆብ ያዕቆብ” ብሎ ለእስራኤል ጠራው። እርሱም፦ “እነሆኝ” አለ። እሱም አለው፦ “የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፥ ወደ ግብጽ መውረድ አትፍራ፥ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና። እኔ ወደ ግብጽ አብሬህ እወርዳለሁ፥ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፥ የዮሴፍም እጅ ዓይንህን ይሸፍናል።” ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ተነሣ፥ የእስራኤልም ልጆች ያዕቆብን ይወስዱ ዘንድ ፈርዖን በሰደዳቸው ሰረገሎች አባታቸውን ያዕቆብንና ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውንም ወሰዱ። እንስሶቻቸውንም በከነዓን አገርም ያገኙትን ከብታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብጽ መጡ፥ ወንዶች ልጆቹንና የልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብጽ ወሰደ። ወደ ግብጽም የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፥ ያዕቆብና ልጆቹ፥ የያዕቆብ በኩር ሮቤል። የሮቤልም ልጆች፥ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ካርሚ። የስሞዖን ልጆች፥ ይሙኤል፥ ያሚን፥ አሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳኡል። የሌዊም ልጆች፥ ጌድሾን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። የይሁዳም ልጆች፥ ዔር፥ ኦውናን፥ ሴላ፥ ፋሬስ፥ ዛራሕ፥ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ፥ የፋሬስም ልጆች ኤስሮም፥ ሐሙል። የይሳኮር ልጆች፥ ቶላዕ፥ ፉዋ፥ ዮብ፥ ሺምሮን። የዛብሎንም ልጆች፥ ሴሬድ፥ ኤሎን፥ ያሕልኤል። ልያ በፓዳን-ኣሪም በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና፥ ሴቲቱ ልጇ ዲና እነዚህ ናቸው፥ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ ሦስት ናቸው። የጋድም ልጆች፥ ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤጽቦን፥ ዔሪ፥ አሮዲ፥ አርኤሊ። የአሴር ልጆች፦ ይምና፥ ይሽዋ፥ ይሽዊና በሪዓ ናቸው። እኅታቸው ሤራሕ ትባላለች። የበሪዓ ልጆች ደግሞ ሔቤርና ማልኪኤል ናቸው። እነዚህ ዐሥራ ስድስቱ ላባ ለልጁ ለልያ በሞግዚትነት ከሰጣት ከዚልፋ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ናቸው፤ እነርሱም ዮሴፍ በግብጽ ምድር ከኦን ከተማ ካህን ከጶጢፌራ ሴት ልጅ ከአስናት የወለዳቸው ናቸው። የብንያም ልጆች፦ ቤላዕ፥ ቤኬር፥ አሽቤል፥ ጌራ፥ ናዕማን፥ ኤሒ፥ ሮሽ፥ ሙፊም፥ ሑፊምና አረድ ናቸው። እነዚህ ዐሥራ አራቱ ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። የዳን ልጅ ሑሺም ነው። የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጼርና ሺሌም ናቸው። እነዚህ ሰባቱ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የሄዱት የያዕቆብ ቤተሰቦች ሥልሳ ስድስት ናቸው፤ ይህም የልጆቹን ሚስቶች ቊጥር ሳይጨምር ነው። ለዮሴፍ በግብጽ ከተወለዱት ከሁለቱ ወንዶች ልጆች ጋር፥ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ቊጥር በአጠቃላይ ሰባ ነበር።