ኦሪት ዘፍጥረት 35:16-29

ኦሪት ዘፍጥረት 35:16-29 መቅካእኤ

ከቤቴልም ተነሡ፥ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፥ በምጡም ተጨነቀች። ምጡም ባስጨነቃት ጊዜ አዋላጂቱ፦ “አትፍሪ፥ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና” አለቻት። እርሷም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን “ቤንኦኒ” ብላ ጠራችው፥ አባቱ ግን ብንያም አለው። ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በምትወስድም መንገድ ተቀበረች፥ እርሷም ቤተልሔም ናት። ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፥ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው። እስራኤልም ከዚያ ተነሣ፥ ድንኳኑንም ከዔዴር ግንብ ባሻገር ተከለ። እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት፥ እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው፥ የልያ ልጆች፥ የያዕቆብ በኩር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ የራሔል ልጆች፥ ዮሴፍና ብንያም ናቸው። የራሔል አገልጋይ የነበረችው የባላ ልጆች፥ ዳንና ንፍታሌም ናቸው። የልያ ባርያ የዚልፋ ልጆችም፥ ጋድ፥ አሴር ናቸው። እነዚህ በፓዳን-ኣሪም በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ መምሬ፥ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት፥ ወደ ቂርያት-አርባ፥ እርሷም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ። ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠ፥ ሞተም፥ ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፥ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}